አቶ ደመቀ መኮንን በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ከአሜሪካና ዴንማርክ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ!

አቶ ደመቀ መኮንን በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ከአሜሪካና ዴንማርክ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ!

– የአውሮፓ ህብረት ልዑክ አዲስ አበባ ገብቷል!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ከሆኑት ጃክ ሱሊቫንና ከዴንማርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄፕ ኮፎድ ጋር መወያየታቸው ተገለፀ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ከሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በስልክ ያደረጉት ውይይት በትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ፣ በህዳሴውን ግድብ፣ ከሱዳን ጋር ባለው የድንበር ጉዳይና ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በሚመለከቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መሆኑ ሲታወቅ፣ አቶ ደመቀ በትግራይ እየተሻሻለ ስላለው ሁኔታ ለጃክ ሱሊቫን ማብራራታቸውና በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ሰሞኑን በተካሄደው በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያም የጋራ ምክክር ማድረጋቸው ተመልክቷል።

የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይን በተመለከተ “በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ያገኛል” ሲሉ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንቱ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ፣ በተመሳሳይ ከዴንማርኩ ው/ጉ/ሚ/ር ጋር ባደረጉት ውይይትም በትግራይ ክልል ያለው የሰብአዊ ድጋፍ በመጀመሪያ ዙር ለ4.5 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ መደረጉንና ሁለተኛ ዙር ድጋፍ መጀመሩን፤ ከተደረገው ሰብአዊ ድጋፍም 70 በመቶው በመንግስት መሸፈኑን ጠቅሰው የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እያደረገ ያለው ድጋፍ እንዲጨምር መጠየቃቸውን ለመረዳት ተችሏል።

በክልሉ ካሉ ጥቂት ቦታዎች በቀር አብዘኛው ቦታዎች ተደራሽ መሆናቸውን፣ የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት ያለገደብ እንዲቀሳቀሱ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን፣ ተፈፀሙ የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የተመድ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ለመመርመር ዝግጅት ማድረጋቸውን እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንም የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ እያደረጉ መሆኑን ለሚኒስትሩ አያይዘው አቶ ደመቀ አስረድተዋል።

የኤርትራ ወታደሮች እንዲወጡ ከኤርትራ መንግስት ጋር ውይይት መደረጉን፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና የአፋር ክልል ልዩ ኃይሎች የህግ በላይነትን ለማስከበር በየአካባቢዎቻቸው እንዲሰማሩ በፌዴራል መንግስት የታዘዙ መሆኑን ከመግለፃቸውም በተጨማሪ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲከናወን ጠንካራ ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ መኖሩን፣ ምርጫውን እንዲታዘቡ የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ለበርካታ አካላት ግብዣ መላኩን፣ እንዲሁም ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብ ጋር ተያይዞ በሁለቱ አገሮች መካከል ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታት የተቀመጡ አሰራሮችና የአለም አቀፍ ህግ በሱዳን በኩል መጣሱን አብራርተዋል።

አቶ ደመቀ በዚሁ ውይይታቸው “የድንበር ውዝግቡ በውይይት ለመፍታት ኢትዮጵያ ዝግጁ ናት። ሱዳን ከሉአላዊ ግዛታችን ለቃ እንድትወጣና ለውይይት ዝግጁ እንድትሆንም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት ማድረግ አለበት” ሲሉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ጄፕ በበኩላቸው መንግስታቸው በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለውን የሰብአዊ ዕርዳታ ለመደገፍ እንዲሁም በሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ እና 6ኛው አገራዊ ምርጫ ዙሪያ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን እንደገለፁ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሀርቪስቶ የተመራው የአውሮፓ ህብረት ልዑክ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን፣ ፔካ ሀርቪስቶ ወደኢትዮጵያ ከመምጣታቸው ከሰዓታት በፊት በቆይታቸው በአዲስ አበባ ከመሪዎች ጋር ከሚያደርጉት ውይይት በተጨማሪ የትግራይ ክልልን ተዘዋውረው እንደሚጎበኙ በትዊተር ገፃቸው አመልክተዋል።

የልዑካን ቡድኑ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ከኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር ተገናኝቶ መምከሩና ፕሬዝዳንቷም ስለትግራይ ሁኔታ ለልዑካኑ ገለፃ ማድረጋቸውን ያሳወቀው የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት፣
“የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ቆይታው በትግራይ ያለውን የዕርዳታ እና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ይመለከታል፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይወያያል፣ ወደ ትግራይ በመሄድ ያለውን ሁኔታ የማየት እቅድ አለው” ሲል አስታውቋል።

ቡድኑ በቆይታው የተረዳውን እና የደረሰበትን ድምዳሜ በሚያዚያ ወር አጋማሽ በሚካሄደው የአውሮፓ ህብረት የሚኒስትሮች ስብሰባ እንደሚያቀርብ ተመልክቷል።

LEAVE A REPLY