ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ “ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት የተነሳችው የግብፅን በአብዮት መታመስ አስልታ ነበር” በሚል መናገራቸው፣ ሀሰተኛና ስልጣናቸውን ለማራዘም የተጠቀሙት እንደሆነ የሀገሪቱ “እውነት አፈላላጊ ተቋም አጋለጠ።
“የአልሲሲ ንግግር ስልጣንን ለማራዘም የተደረገች ብልጣብልጥ ስም ማጥፋት ናት” ያለው በካይሮ የሚገኘው ታዋቂ የግል fact check ኩባንያ “አዲስ አበባ ከግብፅ አብዮት 10 አመታት አስቀድማ በተለይም 2001 ገደማ ጀምሮ ይህንኑ ግድብ ለማስጀመር እንቅስቃሴም ፍላጎትም ነበራት” ሲል አስታውቋል።
“ከግብፅ አብዮት ሁለት ዓመት በፊት ከ2009 ጀምሮ ግብፅ የኢትዮጵያን ህዳሴ ግድብ መገንባት አይቀሬነት ተረድታ ግድቡ በግብፅ የውኃ ድርሻ ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ በመደበኛነት የሚያጠና ኮሚቴ ከመከላከያ፣ ከውጭ ጉዳይ፣ የአገር ውስጥ ጉዳይና ከመስኖና ኤሌክትሪክ መስሪያ ቤቷ የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን በማቋቋም ጥናት ጀምራ ነበር” ሲል የገለፀውና በርካታ ሐሰተኛ ዘገባዎችን በማጣራት የሚታወቀው ይኸው ተቋም “ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ እቅድ አዘጋጅታ ተግባራዊ ያደረገችው ከ2010 ጀምሮ ነው።
ከግብፅ አብዮት 9 ወር ያህል በፊት ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ጥርጊያ መንገድ ጀምራለች። በዚሁ ጊዜም የኢንቴቤውን ስምምነት የዓባይ ተፋሰስ አባል ከሆኑት 5 አገራት ጋር ተፈራረመች፡፡ ይህ ስምምነት በ1929 እና 1959 ለተደረጉት የግብፅ-ሱዳን የናይል ውሃ ውሎች ማብቂያ ነበር” ብሏል።
ሙተሰዲቀ ፋክት ቼክ ኩባንያ ባወጣው በዚሁ ዝርዝር መረጃ “ዊኪሊክስ 2013 ላይ ይፋ ባደረገው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሚስጥራዊ ሰነዶች መሠረት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ 2010 ላይ “ኢትዮጵያ ግድቡን የመገንባት እንቅስቃሴዋን ከቀጠለች በሚል ግብፅ ወታደራዊ ካምፕ በሱዳን እንድታቋቁም (ከአብዮቱ አንድ ዓመት በፊት) ጠይቀዋል፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያ ከአብዮቱ በፊት በነበሩ ዓመታት ግድቡን የመገንባት ፍላጎት ውስጥ ነበረች። ዝግጅቷንም አጠናቅቃለች ማለት ነው” በማለት ገልፆ “የግድቡ እቅድና ከጥር 25ቱ የግብፅ አብዮት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ነው። ከአብዮቱ 4 ዓመታት በኋላ በግብፅ፣ ሱዳንና በኢትዮጵያ የተደረገውን የ2015ቱ የመርህ ስምምነት በመፈረም ለግድቡ ግምባታ ፈቃዳቸውን የሰጡት አል ሲሲ ናቸው። ሌላ የግብፅ መሪ ይህንን አድርጎትም አያውቅም” ሲልም እውነታውን አጋልጧል።
በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያን ዒላማ ያደረጉና መሰረታቸው ግብጽ የሆኑ የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ገጾች እንዲዘጉ መደረጉ ታውቋል።
ፌስቡክ እንዳስታወቀው ከሆነ መሰረታቸውን ግብጽ ያደረጉ ከደርዘን በላይ የግለሰብ አካውንቶች እና ገጾች እንዲዘጉ የተደረጉት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ቱርክን ዒላማ በማድረግ የሚሰሯቸው ስራዎች የፌስቡክን ፖሊሲ የሚቃረኑ ሆነው በመገኘታቸው ነው ተብሏል።
“በተቀናጀ መንገድ ያልተረጋገጠ መረጃ የመስጠት ባህሪ ታይቶባቸዋል” ከተባሉት ከእነዚህ ገጾች ውስጥ 23ቱ የፌስቡክ ገጾችና አካውንቶች እና ሶስት የኢንስታግራም አካውንቶች ሲሆኑ፣ በአማርኛ ቋንቋ የተለያዩ መረጃዎችን ያወጡ እንደነበርና የተባለ ሲሆን ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተለያዩ ወቀሳዎችን በሚያጋሩት ታሪክ ውስጥ ሲያስገቡ እንደነበር ተደርሶበታል ተብሏል።