ኢትዮጵያ ለሁለተኛው የግድቡ ሙሌት ሱዳንና ግብጽ ተወካይ እንዲልኩ ጠየቀች!

ኢትዮጵያ ለሁለተኛው የግድቡ ሙሌት ሱዳንና ግብጽ ተወካይ እንዲልኩ ጠየቀች!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ኢትዮጵያ በመጪው ሐምሌና ነሀሴ ወራት ልታከናውን ያቀደችው ሁለተኛው ዙር የግድቡ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ሱዳን እና ግብጽ ተወካይ በመላክ መረጃዎችን ለመለዋወጥ እንዲቻል በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኩል ሀገራቱን መጠየቋ ተገልጿል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ ለሃገራቱ የውሃ ሚኒስትሮች በጻፉት ደብዳቤ በመጪው ክረምት ከሚጀመረው የግድቡ የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ መረጃዎችን መለዋወጥ እንዲያስችል ሃገራቱ ተወካይ እንዲሰይሙ ጋብዘዋል፡፡

ለሀገራቱ በተላከው በዚሁ የግብዣ ደብዳቤ፣ ኢትዮጵያ ጥሪውን ያቀረበችው ከሶስቱ ሃገራት የተውጣጣው ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ያዘጋጀው የግድቡ የውሃ ሙሌት የጊዜ ሰሌዳ ስምምነትን መሰረት በማድረግ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የግድቡ ግንባታ ሂደትና የክረምት ወቅት መቃረቡ እንዲሁም በተግራባዊና አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑም ተጠቅሷል።

“ተወካዮች መሰየም ትክክለኛ መረጃ ለመለዋወጥ ከማስቻሉም በላይ በአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት በሚካሄደው ድርድር ላይ መተማመንን ለመፍጠር እንደሚያግዝ፣ የግድቡ የውሃ ሙሌት የሚካሄደው ሶስቱ ሃገራት በፈረንጆቹ 2015 በደረሱት የመግባቢያ ሰነድ አንቀጽ ሀ መሰረት እንደሆነ” በደብዳቤው መገለፁንም ለመረዳት ተችሏል።

በሌላ በኩል፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ከፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአውሮፓ ህብረት ልዑክ መሪ ሚስተር ፔካ ሀቪስቶ ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታና በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በስፋት የተነጋገሩ ሲሆን፣ በተለይም ግድቡን በሚመለከት በነበራቸው ውይይት
ኢትዮጵያ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ድርድሩ በውጤት አንዲጠናቀቅረ ላደረጉት ጥረት ከበሬታ ያላት መሆኑን ገልፀው በቀጣይም በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን አቶ ደመቀ መግለፃቸው ተመልክቷል።

በተጨማሪም ድርድሩ በአውሮፓ ህብረት፣ በአሜሪካ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ታዛቢነት እንደሚካሄድ አብራርተው፣ የውሃ ክፍፍል ስምምነት በሶስቱ አገራት መካከል ብቻ የሚካሄድ አለመሆኑን እንዲሁም ረጅም ጊዜ የሚወስድ እንደሆነና ድርድሩ በግድቡ የውሃ ሙሌት ላይ ማተኮር እንዳለበት መናገራቸው ተገልጿል።

ሚስተር ሀቬስቶ በበኩላቸው፣ የህዳሴው ግድብ ድርድር በመጪው ክረምት ከሚከናወነው የውሃ ሙሌት በፊት ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ በአውሮፓ ህብረት በኩልም የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ፍላጎት መኖሩንና የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብን ሁለቱ አገራት በድርድር መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል ተብሏል።

LEAVE A REPLY