የአሜሪካው ኩባንያ “ሮሃ የህክምና ማዕከል” የተሰኘ ሜጋ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው!

የአሜሪካው ኩባንያ “ሮሃ የህክምና ማዕከል” የተሰኘ ሜጋ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በሮሃ ሜዲካል የተባለ የአሜሪካ ኩባንያ “አዲስ አበባን በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የህክምና ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ያስችላል የተባለለትን የሮሃ ህክምና ማዕከል ሊገነባ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 13 አድዋ ፓርክ አካባቢ በ300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባውን የዚህ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይም የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ አስቀምጠዋል።

በ5 ዓመት ይጠናቀቃል የተባለለት የሕክምና ማዕከሉ በውስጡ 5 ሆስፒታሎች እንደሚኖሩት የተገለፀ ሲሆን፣
በየዓመቱ አንድ ሆስፒታል አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ መታቀዱም ተነግሯል።
ሮሃ የሕክምና ማዕከል በውስጡ የነርቭና የጀርባ ፣ የህጻናትና እናቶች፣ የልብ ሕክምና ሆስፒታሎች፣ የሕክምና ትምህርት ቤት እንዲሁም የጥናትና ፈጠራ እና የማገገሚያ ማዕከላት የተባለው ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 4 ሺ 200 የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ለ7 ሺህ 200 ሰዎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።
ማዕከል በውስጡ አምስት ሆስፒታሎችና ከ 1ሺ 100 በላይ አልጋዎች እንዲኖሩትና በዓመት ከአንድ መቶ ሺ በላይ ለሆኑ ታካሚዎች አገልግሎት እንዲሰጥ መታቀዱም ተነግሯል።
በዛሬው የግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶከተር ዐቢይ “ቦታ አጥሮ መቀመጥ አይቻልም፤ ሆስፒታሉ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲያልቅ አስፈላጊው ክትትል ይደረጋል።…ከህክምና ማዕከል ግንባታው ጎን ለጎን መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ስርዓት ተግባራዊ እንዲሆን በከተማዋ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ምቹ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ያስፈልጋል” ያሉ ሲሆን፣ መርሃ ግብሩ ከተጠናቀቀ በኋላም በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው “ዜጎች ተገቢውን የጤና አገልግሎት ያገኙ ዘንድ ተደራሽነቱን ማስፋት በእጅጉ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው። ዛሬ ጠዋት የሮሀ የሕክምና ማዕከል ሰፊ ፕሮጀክት የግንባታ ሥራ መጀመሩ፣ ለዚሁ ቀዳሚ ተግባር የተሰጠውን ትኩረት ያመላክታል። ተጨማሪ 1,200 አልጋዎችን የሚኖሯቸውን 5 ሆስፒታሎች የሚያካትተው የሕክምና ማዕከል ተገንብቶ ሲጠናቀቅ፣ ኢትዮጵያ በሕክምና ቱሪዝም በኩልም ተፈላጊ እንድትሆን ያደርጋታል” ብለዋል።

LEAVE A REPLY