ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– “ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ግዙፍ ሀገር ናት፤ የቀጠናው ሀገራት የደህንነት ጉዳዮች የሚወሰኑት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ነው” ሲሉ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ያቭጋኒ ተርክን ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እና ደህንነት የሚሰፍን ከሆነ የቀጠናው ሰላም እና ደህንነትም የተሻለ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የራሷን እና የቀጠናውን ደህንነት ለመጠበቅ በምታደረገው ጥረት የሩሲያ መንግስት ድጋፍ እንደማይለያትና ሀገራቸው የኒውክሊየር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ተግባር ለማዋል ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሰራ ገልፀዋል።
“የሩሲያ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ደህንነትን ለማጠናከር በተለያየ መንገድ ድጋፍ እያደረገ ነው” በማለት የተናገሩት አምባሳደሩ፣ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያና ሩሲያ ለበርካታ ዓመታት በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውንም አመልክተዋል።
አምባሳደር ያቭጋኒ ተርክን፣ በተለይ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በነበረችበት ወቅት በጉዳዩ ላይ የተለየ ትኩረት በመስጠት መስራታቸውን ጠቁመው “የሀገሪቱን ደህንነት እና ፀጥታ በዋናነት ማስጠበቅ የሚችለው የኢትዮጵያ መንግስት ነው፤ ይህንን መቀበል አለብን። ለዚህም ሩሲያ የኢትዮጵያን የመከላከያ ሃይል ለማጠናከር ሰፊ እርዳታዎችን ሰጥታለች” ብለዋል ።
ሀገራቸው የኒውክሊየር ሃይልን ለሰላማዊ ተግባር ለማዋል ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንደምትሰራ የጠቆሙት አምባሳደሩ “ኢትዮጵያ የኒውክሌር ተጠቃሚ ሃገሮች አባል ከሆነች እኛ ለመርዳት ዝግጁ ነን” በማለትም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደስልጣን በመጡ ሰሞን በሩሲያ ያደረጉትን የስራ ጉብኝት አስመልክተውና በቅርቡ በተካሄደው “የአፍሪካ-ሩሲያ መድረክ” ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ለሰላማዊ ተግባር የሚውል የኒውክሊየር ኃይልን ለማበልፀግ ፍላጎትና ተነሳሰሽነት እንዳላት መግለፃቸው ይታወሳል።