ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በመጪው ሐምሌና ነሀሴ ወራት ሊተገበር ዕቅድ የተያዘበት ሁለተኛው ዙር የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት መረጃ ለመለዋወጥ እንዲቻል ሱዳንና ግብጽ ባለሙያዎችን እንዲሰይሙ የኢትዮጵያ በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኩል ያቀረበችውን ጥሪ ሀገራቱ እንዳልተቀበሉት አስታውቀዋል።
ጥሪውን እንደማይቀበሉ የገለፁት የሱዳን የመስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስቴርና የግብፅ የመስኖ ሚኒስቴር በተናጠል ባወጧቸው መግለጫዎች ሲሆን፣ የሱዳኑ “ከመረጃ ልውውጡ በፊት አስገዳጅ ስምምነት ይኑር። ሂደቱ በአስገዳጅ የህግና የስምምነት ማዕቀፍ ሊደገፍ ይገባል” ብሏል።
ካሳለፍነው ወርሃ ሰኔ ወዲህ በተደረጉ የሶስትዮሽ ድርድሮች 90 በመቶ ያህል ስምምነት ላይ ተደርሶባቸው በረቂቅ ደረጃ ከተዘጋጁ የስምምነት ሃሳቦች መካከል አንዱ የመረጃ ልውውጥ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ ሆኖም ኢትዮጵያ የመረጃ ልውውጡን “ለራሷ በሚስማማት መልኩ ለመቀበል መሻቷን የሚጠቁሙ አጠራጣሪ አዝማሚያዎችን በደብዳቤው ተመልክቻለሁ” በማለትም ጥሪውን እንዳልተቀበለው በይፋ አስታውቋል።
ተመሳሳይ አቋም ያንፀባረቀው የግብጽ መስኖ ሚኒስቴር በበኩሉ “በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር ሙሌት ሊያጋጥም የሚችለውን ችግር በአስዋን ግድብ ባለው ከፍተኛ የውሃ ክምችት ለመቋቋም እንችል ይሆናል፤ ነገር ግን የድርቅ አስተዳደር ጉዳይ አሳሳቢ ነው” ሲል ተናግሮ፣ በኢትዮጵያ የቀረበውን የመረጃ እንለዋወጥ ሃሳብ “አልቀበልም” ብሏል።
በተያያዘ፣ የሱዳን የመስኖ ውሃ ሃብት ሚኒስትር የህዳሴ ግድቡ ሁለተኛ ሙሌት የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ በጀበል-አውሊያ ማጠራቀሚያ 600 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለማከማቸት ስራ እንጀምራለን ብሏል፡፡
“እርስ በርስ የሚጣረሱ አቋሞችን በማንፀባረቅ ይታወቃሉ” የሚባሉት ሚኒስትሩ ያሲር አባስ፣ ባንድ በኩል “ግድቡ እንደሚጠቅመን እናውቃለን።
ግንባታው በኢትዮጵያ በራሷ መሬትና ገንዘብ ማካሄዷን መብቷ ነው ብለን የደገፍነው እኛ ነን” ሲሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ “አሳሪ ስምምነት ሳይደረግ በግድባችንና በናይል ዙሪያ የሚኖረው ሀያ ሚሊዮን ሕዝብ አደጋ ላይ ይወድቃል። አሳሪው ውል ሳይቋጭ ውሀ ሙሌቱ ከተካሄደ የትኛውንም አማራጭ ለመጠቀም እንገደዳለን” ብለዋል።
በቅርቡም የ Talk to Aljazeera አዘጋጁ ጋዜጠኛ ሙሐመድ ቫል ጋር ባደረጉት ቆይታ ላይ “አስረግጬ የምነግርህ ጦርነት ብሎ ነገር አይኖርም። በዓለም ታሪክ ውስጥ የትኛው ሀገር ነው በውሀ ተጣልቶ ጦርነት ውስጥ የገባው? ውሃ በባህሪው መስማምያ እንጂ የጦርነት ሰበብ አይደለምም” ማለታቸው የሚታወስ ነው።