ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ኢትዮጵያ እየሰጠች የሚገኘው የ”አስትራዜኔካ” ክትባት “እየተዛመተ በሚገኘው የተዛባ አመለካከትና የተሳሳተ መረጃ” ምክንያት በተገቢው ጥቅም ላይ እየዋለ አለመሆኑን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
“በተለይ ዕድሜአቸው ከ55 እስከ 64 የሆኑ የማህበረሰቡ ክፍሎች በተገቢው መልኩ ክትባቱን እየወሰዱ አይደለም” ያለው ቢሮው፣ በክትባቱ ዙሪያ የሚሰራጨውን ሀሰተኛ መረጃ በመከላከል እና ህብረተሰቡን በማስተማር በኩል የሀይማኖት አባቶች ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።
“እስካሁን እድሜአቸው ከ55 እስከ 64 ለሆኑ ዜጎች 64 በመቶ ብቻ ነው መከተብ የተቻለው” ሲል የገለፀው ጤና ቢሮው፣ በአዲስ አበባ ከተማ እስካሁን ለ72 ሺ ያህል ዜጎች ክትባት መሰጠቱንም አመልክቷል።
አስትራዜኒካ የተባለው ክትባት ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን አስመልክተን በሰራነው ዘገባ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ የተሰራጨው የተሳሳተ እምነትና የሀሰት መረጃ በክትባቱ ሂደት ላይ እክል ሊፈጥር እንደሚችል መጠቆማችን ይታወሳል።