የሐረሪ ክልልና የምርጫ ቦርድ ውዝግብ አነጋጋሪ ሆኗል!

የሐረሪ ክልልና የምርጫ ቦርድ ውዝግብ አነጋጋሪ ሆኗል!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚገኝ የሐረሪ ተወላጅ ካለበት ሆኖ የጉባኤ አባላትን እንዲመርጥ” በሚል የሐረሪ ክልል ያቀረበውን ጥያቄ፣ ሳይቀበለው መቅረቱን ለማወቅ ሲቻል፤ የቦርዱን ውሳኔ የተቃወመው የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤትም ባለሦስት ነጥብ ውሳኔ ማሳለፉ አነጋጋሪ ሆኗል።

“የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) ሚያዚያ 3/2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሀረሪ ጉባዔን አስመልክቶ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን አስተላልፏል” ያለው የሀረሪ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ የሀረሪ ክልል የምርጫ አፈፃፀም ሂደት በክልሉ የሐረሪ ጉባኤ እና የፌደራል ህዝብ ተወካይ ልዩ ውክልና ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ እንዳልሆነ አመልክቶ “ካቢኔው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሚያዚያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም የሀረሪ ጉባዔን አስመልክቶ ያስተላለፈው ውሳኔ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 6 ቀን 1987 ዓ.ም ባካሄደው 102ኛ መደበኛ ስብሰባ ያሳለፈው ውሳኔን፣ የክልሉ ሕገ መንግስት እና የምርጫ ሕጉን በሚጻረር መልኩ የሰጠው ውሳኔ ሕገ መንግስታዊ ይዘት የለውም፤ እንዲሁም ከሕግ አንጻር ተቀባይነት እንደሌለው ገልጿል” ሲል አስታውቋል።

ቢሮው “ካቢኔው ባካሄደው አስቸካይ ስብሰባ ከዚህ በታች በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አስተላልፏል” በማለትም የውሳኔውን ዝርዝር እንዲህ አስቀምጧል:-
1ኛ.የሀረሪ ክልል ምርጫ አፈጻጸም ሂደትን ፣ የሀረሪ ጉባኤ እና የፌደራል ህዝብ ተወካይ ልዩ ውክልና ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ አለመሆኑን ገልጿል።

2ኛ.የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሚያዚያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም የሀረሪ ጉባኤ ምርጫን አስመልክቶ ያስተላለፈው ውሳኔ ህገመንግስትዊ ፣ ህጋዊ ፣ ፍትሃዊና ፣ አመክንዮያዊ ያልሆነ መሆኑን እንዲሁም የሀረሪ ክልል ሕገ መንግስትን ያላማከለ ስለሆነ ከሕግ አንጻር ተቀባይነት እንደሌለው ጠቅሷል።

3ኛ.የክልሉ ካቢኔ በውሳኔው የክልሉ ሕገ መንግስትና የሕግ የበላይነት እንዲከበር እንዲሁም የፌደራል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላለፈው ውሳኔ ሊከበር እንደሚገባ እና እነዚህን ችግሮች ለማረም አግባብነት ያለው አካል ተቋቁሞ ተገቢው የእርምት እርምጃ እንዲደረግ ወስኗል።

ይሁንና የካቢኔውን ውሳኔ ተከትሎ በህግ ባለሙያዎችና በፖለቲካ ሰዎች አስተያየቶች እየተሰጡበት ሲሆን፣ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት የህግ አማካሪ የሆኑት አቶ ውብሸት ሙላትም ️”የቦርዱ ውሳኔ ሕገመንግሥታዊም፣ሕጋዊም፣ ፍትሐዊም፣ ምክንያታዊም ስላልሆነ ተቀባይነት የለውም” የሚል ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ የቦርዱ ውሳኔ ሕገ መንግሥቱንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔን ማክበር እንዳለበት ገልጾ “እነዚህን ችግሮች ለማረም አግባብነት ያለው አካል ተቋቁሞ ተገቢው የእርምት እርምጃ እንዲደረግ ወስኗል። ” የሚሉት ይገኙበታል።

የሐረሪ ክልል ካቢኔ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ የማሳለፍ ሥልጣን መኖር/አለመኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ፦

1. የምርጫ ቦርድ ለሚሰጣቸው ውሳኔዎች ሕጋዊ ሥርዓት ተከትሎ ቅሬታ/ይግባኝ ማቅረብ እንጂ እንዲህ ዓይነት “እብሪታዊ” ውሳኔ እንዴት ይወሰናል?

2. የምርጫ ቦርድ ውሳኔን አልቀበልም ካለ፣ በአገሪቱ በሙሉ እራሱ ምርጫውን ሊያከናውን ነው? ያለመቀበል ውጤቱ ምንድን ነው? በክልሉ ውስጥ ምርጫ እንዳይደረግ ማወክ? ማነሳሳት? (በክልሉ የመራጮች ምዝገባ እየተካሔደ አይደለም ማለቱን ልብ ይሏል።)

3. የባሰው ደግሞ ተገቢው “የእርምት እርምጃ እንዲደረግ ወስኗል” ማለት፣ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ስህተት መሆኑን በራሱ ወስኖ፣ ከዚያ ባለፈም የእርምት እርምጃ እንዲደረግ መወሰን (ምርጫ ቦርድ የካቢኔውን ውሳኔ ተመልክቶ ውሳኔውን እንዲያርም ይሆን?) የሚገርም ነው።

4. ይህ ውሳኔ የተላለፈው (በክልልም ቢሆን) በመንግሥት መሆኑ የበለጠ አስገራሚ ያደርገዋል። ሕጋዊ ሥርዓትን ተከትሎ ይግባኝ አለማለት፣ አንዱ የመንግሥት አካል ሌላው የመንግሥት አካል ላይ እንዲህ ዓይነት የእብሪት ውሳኔ ማሳለፍ አገሪቱ ያለችበትን አደጋ የሚያሳይ ነው።

ምርጫ ቦርድ ለሚወስናቸው ውሳኔዎች ሌላው ክልል ምን ዓይነት ውሳኔ እንደሚወስን ማየት ነው!” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውበታል።

LEAVE A REPLY