ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ሱዳን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ “ከኢትዮጵያና ግብፅ ጋር በዝግ እንወያይ” በማለት ጥሪ ማቅረቧ፣ በእስር ላይ የነበሩ 61 ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው መመለሷና ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናትን ቁልፍ ድንበሯን መዝጋቷ ተሰምቷል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብደላ ሀምዶክ ለግብፁ አቻቸው ሙስጠፋ ማድቦሊ እና ለኢትዮጵያው ጠ/ሚር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ “በ10 ቀናት ውስጥ በዝግ እንወያይ” የሚል ጥሪ ማቅረባቸው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የተዘገበ ሲሆን፣ በጥሪያቸውም “ከ10 ባልበለጡ ቀናት ውስጥ ተገናኝተን የድርድሩን ሂደቶች እንገምግም” ማለታቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ “በ2015ቱ የመርሆዎች ስምምነት መሰረት ወደፊት ለመራመድ በሚያስችሉን አማራጮች ላይ ተወያይተን እንስማማ፤ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነታችንንም እናድስ” ባሉበት በዚሁ ጥሪያቸው፣ ጥሪውን ለማቅረብ የተነሱት “በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረጉት ተደጋጋሚ የሶስትዮሽ ድርድሮች ውጤታማ ሳይሆኑና ስምምነት ላይ ሳይደረስ ዓመታት በመቆጠራቸው” በመሆኑ እንደሆነ መግለፃቸውም ተመልክቷል።
በሌላ በኩል፣ የሱዳን ጦር ባሳለፍነው ሰኞ “በቁጥጥር ስር አውያቸዋለሁ ያላቸውን 61 ኢትዮጵያውያን አሳልፎ መስጠቱን የገለፀ ሲሆን፣ ርክክቡ የተካሄደውም በአልቃዳሪፍ አቅራቢያ በምትገኘው የከላባት ድንበር ማቋረጫ በኩል መሆኑ ተጠቅሷል።
“ርክክቡ የተካሄደው የሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ነው” ያለው የሱዳን የመከላከያ ሰራዊት መግለጫ፣ 61ዱን ዜጎች ያሰረውና አሳልፎ የሰጠው በደህንነት ስጋት ሳቢያ መሆኑንም አያይዞ ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሱዳን በምስራቃዊ የሀገሯ ክፍል ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር በኮሮና ቫይረስ መጨመር ምክንያት እንደዘጋች ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል።
“በአልቃዳሪፍ ግዛት የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ጨምሯል” ያለው ዘገባው፣ የአልቋዳሪፍ ግዛት በትግራይ ጦርነት የተነሳ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በብዛት የሚገኙበትና 70ሺ የሚደርሱ ስደተኞች የሰፈሩበት እንደሆነ ጠቅሶ፣ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር መጨመር በአልቃዳሪፍ ግዛት ከፍተኛ ስጋት በመፍጠሩ የኢድ ሶላት በመስጊድ ጊቢ ውስጥ ብቻ እንዲደረግ ትዕዛዝ መተላለፉንም አስታውቋል።