ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች በድጋሚ ያገረሸው ግጭት እስከ ከሚሴ መስፋፋቱንና ለህይወታቸው የሰጉ በብዙ ሺዎች የሚገመቱ ሰላማዊ ዜጎች ቀያቸውን ለቀው ለስደት መዳረጋቸውን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
በግጭቱ ምክንያት ከአዲስ አበባ- ደሴ – መቀሌ የሚያደርሰው ዋና መንገድ የተዘጋ ሲሆን፣ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የክልሉ ልዩ ሀይል እና መከላከያ ሰራዊት ከአቅማቸው በላይ እንደሆነባቸውም ተገልጿል።
በአጣዬ ከተማ ከትናንት በስቲያ አንድ መኖሪያ ቤት መቃጠሉን መነሻ በማድረግ እንደገና ባገረሸው የታጣቂዎች ጥቃት የበርካታ ሰዎች ህይወት እያለፈ መሆኑን፣ በኤፍራታ፣ ግድም፣ ቀወትና በአንጻኪያ ወረዳ ስር ባሉት ካራቆሬ፣ ቆሪሜዳ፣ ማጀቴ፣ ካብሰራምባ፣ ገተም ውሃ፣ ኩሪብሪ፣ ዋጮ እና ዘንቦ ቀበሌዎችም ታጣቂዎቹ በከባድ መሰሪያ የታገዘ ጥቃት ማድረሳቸውን ከአካባቢው ነዋሪዎች ከሚደርሰን መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ከትናንት ጀምሮ በተለይም በአጣዬ ከተማ ከባድ የተኩስ ልውውጥ በመደረግ ላይ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎቹ ችግሩ በአካባቢው ካለው ልዩ ሀይል እና መከላከያ ሰራዊት አቅም በላይ መሆኑን ተናግረው፣ ወደነዚህ ቀበሌዎች በመግባት ጥቃት በመፈጸም ላይ ያሉት ታጣቂዎቹ የያዙት የጦር መሳሪያ ዘመናዊ ከመሆኑ የተነሳ ታጣቂዎቹ በመከላከያ ኃይል ላይም እየተኮሱ መሆኑን አመልክተዋል።
“ጥቃቱ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ነዋሪዎቹ አሁን ላይ መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ወደ ሌሎች አጎራባች ቀበሌዎች እና ከተሞች በመሸሽ ላይ ናቸው” ያሉት ነዋሪዎቹ፣ ወደዳር አካባቢ የነበረው የተኩስ እሩምታ ወደ መሃል ክፍልም መዛመቱን ተናግረዋል።
በተያያዘ የሰሜን ሸዋ አስተዳደር “ችግሩ ከአቅም በላይ ሆኖብኛል የፌደራል መንግስቱን ድጋፍ እንፈልጋለን” ያለ ሲሆን፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረ ጻዲቅም “ዛሬ 3ኛ ቀኑን በያዘው የታጣቂዎች ጥቃት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል” ብለዋል፡፡
“መንግስት አስቸኳይ እርምጃ ወስዶ ሀይል ካልመደበ ችግሩ ከዚህም በላይ ይከፋል” ያሉት አስተዳዳሪው
ታጣቂዎቹ የተደራጁ መሆናቸውን ገልጸው፣ ሰዎች ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ነው፣ ቤቶች ወድመዋል፣ ታጣቂዎቹ በተደራጀ መልኩ በመኪና እንደሚመጡ ሰምተናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ግጭቱ ወደሌሎች ከተሞችም እየሰፋ መሆኑን ያመለከቱ ምንጮች በበኩላቸው፣ በከሚሴ የተከሰቱ ታጣቂዎች “በአስቸኳይ ማረሚያ ቤት የታሠሩ የኦነግ ባልደረቦቻችን ካልተፈቱና አድማ ብተና ፖሊስ ካልወጣ ማረሚያ ቤቱን እንሰብራለን!” በማለት ማረሚያ ቤቱን ከበው እንደሚገኙ አስታውቀዋል። ስጋት የገባቸው የከሚሴ ነዋሪዎችም ሙሉ አካባቢያቸውን ለቀው እየተሰደዱ መሆኑ ተመልክቷል።