ሞቷል የተባለው ቲያትር አሸልቦ ተገኘ! || ተስፋዬ ማሞ (ደራሲና አዘጋጅ)

ሞቷል የተባለው ቲያትር አሸልቦ ተገኘ! || ተስፋዬ ማሞ (ደራሲና አዘጋጅ)

ባሳለፍኳቸው 33 የሙያ ዓመታት ውስጥ በአንድም የቲያትር ቤት መድረክ ላይ የቀረበ ቲያትር የለኝም። በአንድም የመድረክ ቲያትር ላይ አልተወንኩም ወይም ቲያትር አላዘጋጀሁም። ስለዚህ በኢትዮጵያ የቲያትር ታሪክ ውስጥ ምንም ሊጠቀስ የሚችል ሥራ የለኝም። ይህ ማለት ግን በልዩ ልዩ ምክንያት ለመድረክ ያልበቃም ቢሆን ለመድረክ ቲያትር ተብሎ የተሰናዳ ፅሁፍ አልነበረኝም ማለት ግን አይደለም። ሞክሪያለሁ ግን አላሳካሁም። ሆኖም ግን ያሳለፍኳቸው 33 ዓመታት በተለይም እስክ 1992 ዓ.ም የነበሩት ጊዜያት ከቲያትር ጋር እጅግ ቅርብ ሆኜ ያሳለፍኩባቸው ዘመናት ናቸው። እኔ ሃሳቤን በቀላሉ አስተላልፍበታለሁ ብዬ በመረጥኩትና ብዙ በሠራሁበት የቴሊቪዥን ድራማም ይሁን በራዲዮ ድራማና የቪዲዮ ፊልም ዘርፍ ቁጥራቸው እጅግ ከበረከተ ተዋንያን ጋር የመሥራት ብዙ ዕድልን አግኝቻለሁ። ከአንጋፋ የመድረክ ሰዎችና ድምጻውያን እስከ ጀማሪ ተዋንያን ጋር አብሬ ሠርቻለሁ። በራሴ ሥራዎች ላይም እንዲሳተፉ አድርጌያለሁ።

እነዚህን በስም ልዘርዝር ብል ልዘልቃቸው አልችልምና አልሞክረውም። ሆኖም ከአብራር አብዶ እሰክ ስዩም ተፈራ ከገድሉ አሰግደው እስከ ተስፋዬ ሲማ …ከጌታቸው አበራ እስከ ወርቅአገኝ ምስጋናው፣ ከጀማነሽ ሰለሞን እስከ አሰገደች አስፋው፤ ከወለላ አሰፋ እስከ እፀገነት ተስፋዬ፤ ከአልማዝ ኃይሌ እሰክ ትእግስት ባዩ፣ ከሰይፈ አርአያ እስከ ተስፋዬ ገ/ሃና ከመዐዛ ብሩ እሰከ ፈለቀ አበበ፤ ከጥላሁን ጉግሳ እስከ አይናለም ተስፋዬና አለምጸሃይ በቀለ…ከአላዓዛር ሳሙኤል እስከ አሰፋ በየነ….ከሽመልስ አበራ እስከ ይገረም ደጄኔ፣ …..ፍጹም ዘርዝሬ ከማልጨርሳቸው በርካቶች ጋር የመሥራትን ዕድል አግኝቻለሁ። እነዚህ የዘረዘርኳቸው ሁሉ በመድረክ ቲያትር ላይ የደመቁና የተጨበጨበላቸው ናቸው። ብዙዎቹም በእኔ ሥራዎች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የቴሊቪዥን ድራማ የመሥራት አጋጣሚን ያገኙ ናቸው።
ስለዚህ ቲያትር ሲወሳና ሲከበር ራሴን የዚያ ክብረ በዓልና ታሪክ አካል አድርጌ አስባለሁ። በብዙ ኹነቶች ውስጥ አብሬ አልፌያለሁ። ከሰሞኑ የቲያትር 100ኛ ዓመት ሲከበር በብዙ ትዝታዎች ተጥለቅልቄያለሁ። ብዙ ቲያትሮችንና ብዙ ተዋኞችን አስታውሻለሁ።
በሸራተን አዲስ በነበረው የቲያትር 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ታድሜ የዕለቱን ግሩም ዝግጅቶች ስመለከት እነዚህ ትዝታዎች ሁሉ በዐይኔ ላይ አልፈዋል። “ሼክስፒር ኢትዮጵያዊ ነው”ን ስመለከት፣ ሀረገወይን አሰፋን ከአፍላ ወጣት የልጅነት ዘመኗ ጀምሮ ያየኋቸውንና ከእኔ አልፎ በልጆቼ ዘመን ላይ የደመቀውን ችሎታዋን ሳይ እንደሁሌው ሁሉ ዛሬም ተደምሜለሁ። ተስፋዬ ገብረሃናና መሠረተ ህይወት ያሳዩት ድንቅ አተዋወን ቲያትር ሞቷል ለሚሉ በመሞትና በማሸለብ መሃል ያለውን ሰፊ መስመር እንዲረዱና ተወራራሽነት እንጅ በጠቢባን ሥራዎች ሞት የሚባለው አንጻራዊ ብቻ መሆኑ የዕድሜ ዘመን መማሪያ ይሆናቸዋል። ሳማሶን ታደሠን ጨምሮ ያሉት ወጣት ተዋንያን በዕለቱ ያሳዩት ብቃትም ማሸለብን እንጅ ሞትን እንደማያሳዩ አረጋግጠዋል።
የእንዳለጌታ ከበደ የብዕር ትሩፋትና የመኩሼዬ ተስፋዬ እሸቱ ዝግጅት የሆነው “የካሣ ፈረሶች” ለከረመው የሳቅ ጠኔዬ ጥሩ ማካካሻና መፈወሻ ሆኖኛል። በዘመን ኮቪድ ለታፈነውና ለዛገው ጭፍጋጋ ውስጣዊ ስሜቴ ጥሩ ማስተንፍሻ ክትባት ነበር። የትውና ችሎታውን ገና ተማሪ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ በማንያዘዋል እንደሻውና ተፈሪ አለሙ ሥራዎች የተዋወቅኩት አለማዬሁ ታደሠ የወይን ጠጅ ነበረ። የእሱ መንፈስ ዙሪያውን ሲያነቃና ሲጋባ በገሃድ ይታይ ነበር። ተጣማጁ ንግስት ወጣቷ መስከረም አበራም የቲያትር ሞት ሳይሆን ህያውነት ሸጋ ማስረጃ ነበረች። ፍቃዱ ከበደን ጨምሮ በካሳ ፈረሶች ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች የሚነግሩን ደማቅ መልዕክት የቲያትር ሞትን ሳይሆን የሸለብታውን ሚስጥርና ከሸለብታው ፈጥኖ ነቅቶ በዘውትራዊው ዐውድ ላይ ሳይደበዝዝ ሊኖር የሚችልበትን መንገድ እንድንመረምር ነው።

ይህ ዕንቆቅልሽ ሆኖብን የከረመውን የ’ለምን? ቲያትር ደከመ” ጥያቄ በከፊል የመለሰልን ክብረ በዓል ‘አይችሉም’ ‘ይጀምራሉ እንጅ አይጨርሱም’ በሚባለው ከባቢ ጨርሰውም፣ ጎል አስቆጥረውም፣ አስጭብጭበውም፣ ተስፋችንን ስላንሰራሩልን እገሌ ከእገሌ ሳይባል አዘጋጆቹ ሁሉ ኮፍያ ሊነሳለቸው ይገባል። እኔ አንስቸላቸዋለሁ!! ትልቁን የቲያትር ሙያ በቦታው መልሰው አሳይተውናለና ክብራቸው ከፍ ይበልልን!!

ትውስታ ዘ ቲያትር 100ኛ ዓመት

 

LEAVE A REPLY