– የወላይታ ከነማ ተጫዋቾች ለገንዘብ ችግር ተዳርገዋል!
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– እየተካሄደ ባለው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አሸናፊ የሚሆነው ክለብ የ1ሚሊዮን ብር ተሸላሚ እንደሚሆን ሲገለፅ፣ ከዚህ ቀደም ሲሰጥ የነበረው የ150 ሺህ ብር ሽልማት በአንድ ጊዜ ወደ 1ሚሊዮን ብር ማደጉ በተሳታፊ ቡድኖች ዘንድ ደስታን መፍጠሩ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በ2013 የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ የሚሆነው ክለብ ከሚሸለመው ዋንጫ በተጨማሪ የ1 ሚሊዮን ብር፣ ሁለተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀው ክለብ የ700 ሺህ ብር እንዲሁም 3ኛ ሆኖ የሚጨርሰው ክለብ ደግሞ የ500 ሺህ ብር ሽልማት ይሰጣቸዋል።
“ፕሪሚየር ሊጉ ሳይጠናቀቅ አሸናፊው ከታወቀ ዋንጫው ለአሸናፊው ቀድሞ ይሰጣል” ያለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር፣ ፕሪሚየር ሊጉ ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚጠናቀና ግንቦት 21 በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤም የኮከቦች ሽልማት እንደሚከናወን አስታውቋል።
ምንም እንኳን ለፕሪሚየም ሊግ አሸናፊዎች ሲሰጥ የቆየው የ150 ሺህ ብር ሽልማት በአንድ ጊዜ ወደ 1ሚሊዮን ብር ማደጉ በተሳታፊ ቡድኖች ዘንድ ደስታን የፈጠረ ቢሆንም፣ በዛሬው ጊዜ ክለቦች ካለባቸው ከፍተኛ የገንዘብ (በጀት) ዕጥረት አንፃር ግን “በቂ ነው” የሚባል አይደለም።
“ሽልማቱ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው የሚከፍሉትን አመታዊ የደመወዝ በጀት እንኳን በአግባቡ የሚሸፍን አይደለም” ሲሉ አስተያየት የሰጡ አንድ የስፖርት ባለሙያ “ክለቦች ለተጫዋቾች ቀለብ፣ ለካምፕ ኪራይ፣ ለትጥቅ፣ ለትራንስፖርትና ለልዩ ልዩ ዕለታዊ የክለብ እንቅስቃሴዎች የሚያወጡት ወጪ ሲደመር፣ ሽልማቱ የቱንም ያህል በአንዴ ማደጉ ያን ያህል አያስገርምም” በማለት፣ የሽልማት ገንዘቦችን በብዙ እጥፍ ማሳደግና ለዚህም በአገር ውስጥና በውጪ ጠንካራ የፋይናንስ ምንጭ ያላቸውን ስፖንሰር አድራጊ ተቋማት ማፈላለግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የወላይታ ሶዶ ከነማ ተጫዋቾች “የ7 ወር ደመወዝ አልተከፈለንም። የበላይ አካላትን እንድናገኝ አይፈለግም፤ ለችግሩ መፍትሄ ይሰጡናል ብለን ብንጠብቅም ሊሆን አልቻለም። ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽን ብንወስደው በቀጥታ ክለቡ ላይ ነው እርምጃ የሚወሰደው ይህ ደግሞ እንዲሆን ባለመፈለጋችን እስካሁን ለችግር ተዳርገን እንገኛለን ” የሚል ቅሬታ በማቅረብ ላይ መሆናቸው ተሰምቷል።
“እኛ ክለቡን ማገልገል፣ የወጣንበትን አካባቢ እና ማህበረሰብ በእግር ኳሱ መወከል ነው ፍላጎታችን። ነገር ግን ለሰባት ወራት ምንም ደመወዝ ሳናገኝ በዚህ መልኩ መቆየታችን አሳዝኖናል” አሳዝኖናል የሚሉት ተጨዋቾቹ፣ ችግሩ ዛሬም ድረስ ሊፈታና ተፅዕኖውም ከአቅማቸው በላይ እየሆነ በመሄዱ ጉዳዩን በሚዲያ እንዲነገር ወደማድረግ ሊወስዱት እየተዘጋጁ መሆናቸውንና ነገሮች አላስፈላጊ መልክ ከመላበሳቸው በፊት የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉላቸው ደጋግመው በመጠየቅ ላይ እንደሚገኙ ከክለቡ የውስጥ ምንጮች የተገኘው መረጃ ያስረዳል።