ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በልደታ ክፍለ ከተማ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ የቦንብ ፍንዳታ የሁለት ግለሰቦች ህይወት ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ሚትሮሎጂ ፊት ለፊት ለልማት በተዘጋጀ ቦታ ላይ ትናንት ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ በተከሰተው የቦንብ ፍንዳታ የሁለት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ አንድ ግለሰብ በፅኑ ተጎድተው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን በልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መርማሪ የሆኑት ረዳት ኢንስፔክተር ዳንኤል ታፈሰ ገልፀዋል፡፡
ረዳት ኢንስፔክተር፣ የምርመራ መዝገቡን ዋቢ አድርገው እንዳብራሩት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አካባቢ አንድ በግምት ዕድሜው ከ50 እስከ 55 የሚገመት ግለሰብ ከሁለት በተመሳሳይ የዕድሜ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሁለት ሴቶች ጋር እየተገፈታተረ ወደ ቦታው ከገባ በኋላ ፍንዳታ መሰማቱና ጉዳት መድረሱ ተረጋግጧል።
“አደጋው እንደተከሰተ ወዲያውኑ የአዲስ አበባ እና የፌደራል ፖሊስ የቴክኒክና የፈንጂ አምካኝ ባለሙያዎች ቦታው ላይ ፈጥነው በመድረስ ተጨማሪ ፍንዳታ እንዳይከሰት አካባቢውን ነፃ የማድረግ ስራ ሰርተዋል” ያሉት ረዳት ኢንስፔክተር ዳንኤል ታፈሰ፣ በተደረገው ፍተሻ በአንደኛው ሟች ኪስ ውስጥ ተጨማሪ ያልፈነዳ ቦንብ መገኘቱንም አስታውቀዋል።
የግለሰቦቹ ማንነት እና የፍንዳታውን ምክንያት ለማወቅ
“ፖሊስ ምርመራ እያደረገ ነው” ተብሏል።