ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአማራ ብሐራዊ ንቅናቄ – አብን “ሕዝባችን ላይ የጅምላ ፍጅት እየተፈጸመ የምርጫ ክርክር አናደርግም” በሚል በኢቲቪ የሚካሄደውን የምርጫ ክርክር ረግጦ መውጣቱ ታውቋል።
በቀጣይ ለሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ የፖለቲካ ፖርቲዎች የምርጫ ክርክር በማድረግ ላይ በነበሩበትና ዛሬ ሚያዚያ 12 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተዘጋጀው የክርክር መድረክ ላይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው የተገኙት አቶ የሱፍ ኢብራሒምና አቶ ጣሂር መሐመድ “በአማራ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጅምላ ፍጅትና ሰቆቃ ተጠናክሮ በቀጠለበት በዚህ ወቅት በክርክር ኺደቱ ላይ ለመሳተፍ እንደማይቻላቸው” በመግለፅ መድረኩን ረግጠው ወጥተዋል።
በዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በማስመልከት “ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጋረጠበትን መንግስታዊ ሽብር በተደራጀ አግባብ እንዲከላከል ጥሪ እናቀርባለን” ሲል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የአቋም መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል።
በመግለጫው ትግሉን ከፊት ሆኖ እንደሚመራ ያሳወቀው አብን ባስተላለፈው አዲስ መልዕክት “የአማራ ሕዝብ በገንዛ አገሩ ውስጥ እንደጠላት ተቆጥሮ የተከፈተበትን የተደራጀና የተቀናጀ መጠነ ሰፊ የዘር ማጥፋት ዘመቻ በማያወላዳ መልኩ የመቀልበስ እንቅስቃሴ በይፋ ጀምሯል ብሏል።
ይህ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ እንዲጀመር የፌዴራሉም ይሁን የክልሉ መንግስት በሕዝባችን ላይ ሳያባራ ለሦስት አመት የቀጠለው የጅምላና የተናጥል ግድያ እንዲሁም ጅምላ ማፈናቀልን ለማስቆም ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌለ ገለጿል።
ችግሩ መንግስታዊ ዘመቻና ስምሪት የሚሰጥበት መሆኑ በተጨባጭ የታወቀ ኃቅ በመሆኑ ጭምር ነው። ያለው የአብን አቋም መግለጫ የተጀመረው ሕዝባዊ ሰላማዊ ትግል የግዴታ ዘላቂ እልባት በማምጣት መቋጨት ይኖርበታል” በማለት አስታውቋል።
“በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ላይ ባልተቋረጠ መልኩ የሚፈፀሙት መንግስት መራሽ የዘር ፍጅቶች በገለልተኛ ኮሚሽን በጥልቀት ተጣርተው በቀጥታ በጥቃት ውስጥ የተሳተፉ፣ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ፣ መንግስታዊ መዋቅርን ለጥቃት ማስፈፀሚያነት ያዋሉ፣ ያስተባበሩና የተመሳጠሩት አካላት ማንነት ለሕዝብ በይፋ እንዲገለፅና ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቋል።
አጠቃላይ ተጎጅዎችን በተመለከተ ተጣርቶ ዝርዝር ሪፖርት ይፋ እንዲደረግ” ሲል ያመለከተው አብን፣ ከሰልፎቹ ዋና ዋና አላማዎች አንዱ “በተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ሕዝብ ላይ ያንዣበቡ ዘር ተኮር ጥቃቶች ፍፁም የማይደገሙ ስለመሆናቸው የማያወላዳ ማረጋገጫ እና የደኅንነት ዋስትና በይፋ እንዲሰጥ ማስቻል” መሆኑንም ገልጿል።