ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮጵያ፣ በተለያዩ ምክንያቶች እየተጀመረ የሚቋረጠውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድርን መልሶ ማስቀጠል እንዲቻል በህዳሴው ግድብ ላይ የሚመክር የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እንዲጠራ ጠየቀች።
ኢትዮጵያ ይህን ሃሳብ ያቀረበችው በቅርቡ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ተደራድረው ስምምነት ላይ መድረስ ላልቻሉት የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና ግብጽ መሪዎች “ተገናኝተን በዝግ እንወያይ” ሲሉ ላቀረቡት ጥሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሰጡት ምላሽ ላይ መሆኑም ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከአንድ ሳምንት በፊት ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ለደረሳቸው ደብዳቤ ምላሽ በሰጡበት ደብዳቤ “በግድቡ ዙሪያ የተካሄደው ውይይት እንዳልተሳካ መቁጠር አግባብ አይደለም” ማለታቸውንና ለዚህም የመርሆዎች ስምምነት መፈረም እና የብሔራዊ ገለልተኛ የሳይንስ ምርምር ቡድን መመስረቱ የድርድሩ ውጤት መሆኑን መጥቀሳቸውን የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።