ከፍተኛ የጤና ቀውስ የሚያስከትሉ መድኃኒቶች በአገሪቱ እየተሰራጩ መሆናቸው ተጠቆመ!

ከፍተኛ የጤና ቀውስ የሚያስከትሉ መድኃኒቶች በአገሪቱ እየተሰራጩ መሆናቸው ተጠቆመ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ከፍተኛ የጤና ቁውስ የሚያስከትሉና በዓለም አቀፍ ደረጃ በአደገኝነት የተፈረጁ ምንም ፈዋሽ ንጥረ ነገር የሌላቸው ወይም የተሟላ ፈዋሽ ንጥረ ነገሮች የሌሏቸው መድኃኒቶች በህገ ወጥ መንገድ በአዲስ አበባ ከተማ ጭምር እየተሰራጩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ።
ህዝቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

“ህብረተሰቡ በተሳሳተ ግንዛቤ ከውጭ የሚገቡትን መድኃኒቶች ጥራታቸው አገር ውስጥ ከሚመረቱት የተሻሉ ነው ብሎ ያምናል። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ችግሩን ለመቅረፍ በተደረገው ጠንካራ የቁጥጥር ሥራ ንጥረ ነገሮቻቸው ከደረጃ በታች የሆኑ መድኃኒቶች በአገሪቱ 8 በመቶ መሆናቸውን ተለይቷል” ያሉት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሄራን ገርባ፣ እነዚህ መድኃኒቶች በድንበር አካባቢዎች በተለይ በሱማሌ ድንበር በኩል በህገ ወጥ መንገድ የሚገቡ እንደሆኑም አመልክተዋል።

“እነዚህ መድኃኒቶች ንጥረ ነገሮች ስለሌላቸው ለሞት የሚያዳርጉ አሊያም መድኃኒት የማይገኝላቸውን ሌሎች በሽታዎች የመፍጠር አቅማቸው ከፍተኛ ነው። ህብረተሰቡ የችግሩን አደገኝነት በመረዳት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት” በማለት ያሳሰቡት ወ/ሪት ሄራን፣ በአየር መንገድ በኩልም በድብቅ የሚገቡ መኖራቸው እንደተደረሰበትም ተናግረዋል።
ስርጭቱን በቀላሉ ለመግታት አለመቻሉን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሯ “ነጋዴዎቹ ህገወጥ መድኃኒቶቹን በድብቅ በስልክና በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት በሚስጥር እያሰራጩ በመሆናቸው ለመቆጣጠር ከባድና ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ጉዳይ ባለመሆኑ የሁሉም ህብረተሰብ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

LEAVE A REPLY