ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ በቤኒንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ ከማሺ ዞን የሚገኘውና ከሃያ አምስት ሺህ በላይ ነዋሪዎች የሚገኙበት የሴዳል ወረዳ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ፣ ከሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መዋሉን፣ በርካታ ነዋሪዎች፣ የወረዳው አስተዳደር እና ፖሊስ አካባቢውን ጥለው መሸሻቸውን እንዲሁም ታጣቂ ቡድኑ ንብረቶችን ማቃጠሉ፣ ነዋሪዎችን፣ አመራሮችን እና የመንግስት ሰራተኞችን መግደሉንና ማገቱን አስታውቋል።
ኢሰመኮ በዚሁ መግለጫው “ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በአቅራቢያው ያለው የፀጥታ ኃይል ከአቅሙ በላይ እንደሆነበትና ተጨማሪ የተላከው ኃይልም ወደ አካባቢው እንዳልደረሰ ገልፀዋል። ይህ ክስተት በክልሉ የቆየው የጸጥታ ችግር እየተባባሰና መልኩን እየቀየረ መምጣቱን የሚያሳይ በመሆኑ ከፍተኛ ስጋት የሚያሳድር ነው” ብሏል።
ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ እና ከሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግስት አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን የገለፀው ኢሰመኮ፣ በቤኒንሻንጉል ካማሺ ዞን የሚገኘው የሴዳል ወረዳ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መዋሉንም አስታውቆ “መንግስት በአፋጣኝ የአካባቢው እና የክልሉን የፀጥታ ኃይል እንዲያጠናክርና ተጨማሪ የሰዎች ሞት እና የከፋ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዳይከሰት እንዲከላከል” ሲልም ጥሪ አቅርቧል።