ሶስት የብልፅግና ዕጩዎች መንግስትን አስጠነቀቁ!

ሶስት የብልፅግና ዕጩዎች መንግስትን አስጠነቀቁ!

– “ዘር ተኮር ጥቃት ይቁም!” የተቃውሞ ሰልፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል!
– የጎንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ምሳቸውን ጥለው ወጡ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በተደጋጋሚ ጊዜ፣ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ እየተፈወመ ያለውን ዘር ተኮር ጥቃት የሚያወግዙ የተቃውሞ ሰልፎች ዛሬም በበርካታ የክልሉ ከተሞች ሲካሄድ ውሏል።

ከተለያዩ አካባቢዎች ከደረሱን መረጃዎች ለመረዳት እንደተቻለው፣ ላለፉት አራት ቀናት በክልሉ ከተሞች ሲካሄዱ ከቆዩት የተቃውሞ ሰልፎች ጋር ተመሳሳይ አቋም የተንፀባረቀባቸውና በአማራ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ዘር ተኮር ጭፍጨፋ እና መፈናቀል እንዲቆም የሚጠይቁ ሰልፎች ዛሬም በደብረ ታቦር፣ በእብናት፣ በጋይንት ነፋስ መውጫ፣ በደጀን፣ በዳንግላ፣ በቡሬ፣ በአማራ ሳይንት፣ በእንጅባራ፣ በአዲስ ቅዳም፣ በቲሊሊ እና ምንጃር ከተሞች ሲካሄዱ መዋላቸውን ለመረዳት ተችሏል።

በተመሳሳይ፣ ትናንት የአደባባይ ተቃውሞ ያስተናገደችው የጎንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም “በአማራ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይቁም። የምንፈልገው ሰላምና ደህንነት እንጂ ምግብ አይደለም” በሚል የቀረበላቸውን የምሳ ሰዓት ምግብ ጥለው ከካፌ በመውጣት ተቃውሟቸውን እንደገለፁ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያስረዳል።

በሌላም በኩል፣ ዘርን መሰረት አድርገው የሚፈፀሙ ጥቃቶች ይቁሙ ከሚሉት ሰልፎች ጋር ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ሌሎች እርምጃዎችም በክልሉ ተወላጆች እየተወሰዱ ሲሆን የመንግስት ሹመት ያላቸው ሰዎች ጭምር የ”ጥቃት ይቁም” ህዝባዊ ንቅናቄን በመደገፍ የየራሳቸውን እርምጃ መውሰድ መጀመራቸው እየተነገረ ይገኛል።

በዚህም መሰረት “በመንግስት ድጋፍ ጭምር በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ወረራ እና የዘር ማጥፋት ካልቆመ ከምርጫው ራሳችንን እናገላለን” ሲሉ ሶስት የገዢው ፓርቲ ብልፅግና ዕጩ ተወዳዳሪዎች ማስጠንቀቃቸው ተሰምቷል።

ከነዚህም መካከል አንዱ የሆኑት የሰብአዊ መብትና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ “የልዩነት ሀሳቤን በመያዝ በመጭው ምርጫ ብልጽግናን ወክየ ለአዲስ አበባ ም/ቤት አባልነት ለመወዳደር በዕጩነት ለመቅረብ ተስማምቼ ተመዝግቤያለሁ። ይህን ያደረግሁበት ምክንያት አንድም ብልጽግና የመሻሻል ዕድል ካለው በውስጣቸው ሆኜ የሚፈጽሙትን ችግር በድፍረት ለመታገል፣ ሁለትም ለህዝባችን ድምጽ ለመሆን ነበር” በማለት ገልፀው፤ ይሁንና ” በየትኛም የአገሪቱ አካባቢ በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈጸመው ጭፍጨፋና ማፈናቀል በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በጨዋነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በየከተሞቹ ሰልፍ የወጣው የአማራ ሕዝብ ድምጽ የማይሰማ ከሆነ እና ጥያቄውም ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶት በአፋጣኝ ካልተመለሰ ራሴን ከዕጩ ተወዳዳሪነት እንዳገል የምገደድ መሆኔን ከወዲሁ ለማሳወቅ እወዳለሁ” ሲሉ ወቅታዊ አቋማቸውን በፌስቡክ ገፃቸው አስታውቀዋል።

እንደ ዶ/ር ሲሳይ ሁሉ፣ የሸዋ እንሳሮ ብልፅግና እጩ የሆኑት ዶ/ር ደረጀ ተ/ማርያምና ብልፅግና ፓርቲን ወክለው በአዲስ አበባ የየካ ክፍለ ከተማ የምርጫ ተወዳዳሪ የሆኑት ዶ/ር ካሳ ተሻገርም ተመሳሳይ አቋም ማንፀባረቃቸው ተነግሯል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ወቅታዊ የክልሉን ሁኔታ አስመልክተው ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ “የአማራ ሕዝብን ሞትና መፈናቀል ለማስቆም ጥረት እየተደረገ ነው፣ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋርም በጋራ እየሠራን ነው” ሲሉ ገልፀዋል።

“በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ላይ ጥቃት ሲፈጸም ቆይቷል። በተለይ በኦሮሚያ ክልል በወለጋና በመተከል አካባቢዎች ሕዝባችን እረፍት የሚነሳ ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል። በተለይ ኦነግ ሸኔ ለዚህ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል” በማለት በመግለጫቸው የጠቀሱት አቶ አገኘሁ “በጥቃቱ የመንግሥት መዋቅር ጭምር ተሳትፏል። … እኛም መዋቅራችንን እየፈተሽን ነው፣ ይህ ሁሉ ውድመት ሲከሰት የጸጥታ ኀይላችን የት ነበር፣ የመረጃ እና የደኀንነት መዋቅራችን የት ነበር የሚለውን እያጣራን ነው” ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘውም “ሰሞኑን በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞን በደረሰው ጥፋት ጥቃት ፈፃሚዎችን ለሕግ ለማቅረብ ከፌዴራል የጸጥታ ኀይል ጋር በጋራ እየተሠራ ነው። የፌዴራል የጸጥታ ኀይልም በጉዳዩ ላይ መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም የምናደርገውን ትግል በማገዝ ከጎናችን እንዲቆም” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

LEAVE A REPLY