ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ መራዘምን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ “የመራጮች ምዝገባ በግማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ዘግይቶ በመጀመሩ፤ በጊዜው በተጀመረባቸው ቦታዎችም በመራጮች ምዝገባ መረጃዎች እጦት እና በሌሎች ምክንያቶች ለመመዝገብ ጊዜ በመውሰዱ የመራጮች ምዝገባ መራዘሙን አሰታወቀ።
የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ በቀሩት ጥቂት ቀናት በአንድ ምርጫ ጣቢያ 1500 ሰው ብቻ መመዝገብ በመቻሉ የተነሳ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በሚገኙ የተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባ በመቋረጡ እና ተጨማሪ ምርጫ ጣቢያዎች በመክፈት ሂደት ክፍተት በመፈጠሩ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ እንዲራዘም ወስኗል” ሲል ገልጿል።
ታቅዶ በነበረው የአፈፃፀም መርሃ ግብር መሰረት የመራጮች ምዝገባ ሚያዝያ 15 እንደሚጠናቀቅ
ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ የጠቀሰው የቦርዱ “የመራጮች ምዝገባ እጅግ ዘግይቶ በጀመረባቸው በአፋር እና በሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ ለሶስት ሳምንት ተራዝሟል ።
ይህም ማለት የመራጮች ምዝገባ ግንቦት 06 ቀን 2013 የሚጠናቀቅ ይሆናል ማለት ነው። የመራጮች ምዝገባ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በተስተጓጎለባቸው ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ለሁለት ሳምንት ተራዝሟል፤ ይህም ማለት የመራጮች ምዝገባ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 የሚጠናቀቅ ይሆናል ማለት ነው።
የመራጮች ምዝገባ እስካሁን ባልተጀመረባቸው እና የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩ እና ቄለም ወለጋ የመራጮች ምዝገባን የማስጀመር እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል” በማለትም አስታውቋል።
“በጥቅሉ ሲታይም እስከ ትላትንና ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 18 ሚልዮን 427 ሺህ 239 ዜጎች (18,427,239) የተመዘገቡ ሲሆን በ41,659 ምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን እየመዘገቡ ይገኛሉ” ሲል አያይዞ የገለፀው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ፓለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎችና ሲቪል ማህበራት የመራጮች ምዝገባን ለማበረታታ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲቀጥሉም ጥሪውን አቅርቧል።