ሰውን ከወደቀበት የበደል ጉድጓድ ያወጣው ዘንድ እግዚአብሔር ክንዱን ወደ ዓለም ላከ፡፡
ሰው ኾኖ የተገለጠው የእግዚአብሔር ክንድ በትሕትና ሁለተኛ አዳም ኾኖ በለበሰው ሥጋ በጉድጓድ ተጥሎ፤ በሥጋ፣ በነፍስ፣ በውስጥ፣ በአፍአ ቆስሎ የነበረ አዳምን ከሞተ ነፍስ አድኖታል፡፡ ከእርሱ አስቀድሞ ሰውን ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከባርነት ወደ ነጻነት የሚያመጣ ባለመኖሩ ዅሉን የፈጠረ፣ ዅሉን የሚያኖር እግዚአብሔር በለበሰው ሥጋ ሞቶ ለሰው ልጅ መድኃኒት ኾነ፡፡ በዚህም “መድኃኒተ ፈነወ እግዚአብሔር ለሕዝቡ፤ እግዚአብሔር ለሕዝቡ መድኃኒትን ላከ፤” ተብሎ በነቢዩ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ (መዝ. ፻፲፥፱)፡፡
ክርስቶስ ባለ መድኃኒት ኾኖ በኃጢአት ለታመሙ ደቂቀ አዳም ዅሉ ሕይወትን ይሰጥ ዘንድ ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡ በምድራዊ ሥርዓት እንደምናየው መድኃኒትና ባለ መድኃኒት እንደሚለያዩት አይደለም፡፡ እርሱ በመምጣቱ (ሰው በመኾኑ) ሁለቱንም ፈጸመ እንጂ፡፡ መድኃኒት አድርጎ ሥጋውን ደሙን የሰጠ እርሱ ነው፡፡
በካህናት አድሮ ሰው በንስሐ ሲመለስ መድኃኒት ወደ ኾነው ወደ ራሱ የሚመራም እርሱ ነው፡፡ በእመቤታችን ማኅፀን የተጀመረው የክርስቶስ መድኃኒትነት እና ፍቅሩ ፍጻሜውን ያገኘው በሕማሙ እና በሞቱ ነው፡፡ መሐሪ ንጉሥ እርሱ መኾኑን ይገልጥ ዘንድም በፈቃዱ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡
ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ከመግባቱ አስቀድሞ ከኢየሩሳሌም ፲፮ ያህል ምዕራፍ በምትርቀው በቤተ ፋጌ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ነበር፡፡ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለቱን ማለትም ጴጥሮስን እና ዮሐንስን “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሒዱ፤ ወደ እርሷ ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበትን ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ፤” በማለት አዘዛቸው (ማር. ፲፩፥፪)፡፡
ሰው ወዳልገባባት የተዘጋች የምሥራቅ ደጅ ወደ ምትባል ወደ ድንግል መጥቶ ዘጠኝ ወር ማኅፀኗን ከተማ አድርጎ እንደ ኖረ፤ ማኅየዊት ከምትኾን ሕማሙ በኋላም ሰው ባልተቀበረበት መቃብር እንደ ተቀበረ፤ አሁንም ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት ማንም ሰው ያልተቀመጠባቸውን፣ አህያንና ውርንጫን እንዲያመጡ ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ፡፡
የፍጥረት ዅሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ እስትንፋሷን የገበረችለትን አህያ አሁን ደግሞ በፈቃዱ ስለ ሰው ዅሉ ሊሞት ሲል ንጉሥነቱን ሊያስመሰክርባት ወደደ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ካለው ፲፮ ምዕራፍ ዐሥራ አራቱን በአህያ ላይ ሳይቀመጥ በእግሩ ተጓዘ፡፡ ከዚያም ሁለቱን ምዕራፍ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ከሔደ በኋላ ወደኢየሩሳሌም በውርጫዋ ላይ ኾኖ ተመለሰ፡፡ በዚህም ሕግ በተሰጣቸው አይሁድ እና ሕግ ባልተሰጣቸው አሕዛብ ላይ እኩል ቀንበርን መጫን እንዳይገባ አጠየቀ፡፡
ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባም እርሱን የሚከተሉት ሰዎች “ሆሣዕና በአርያም” እያሉ ያመሰግኑት ነበር፡፡
እነሆ ሆሣዕና! “ሆሣዕና” በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራው ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ (ዋዜማ) ነው።
ሆሣዕና አስቀድሞ ካለው ረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተክርስቲያን የበዓል ቀን ሲሆን፣ በዚሁ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ “ሆሣዕና በአርያም… ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት… ዕለተ ሆሣዕናሁ አርዓየ… ወዘተ በማለት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ቅዱስ፣ ያሬድና ሌሎችም አባቶች በየቦታው እየጠቀሱና እየተዘመሩለት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘመር፤ ይህ ሰንበት በጌትነትና በክብር፣ በውዳሴና ቅዳሴ ሆሣዕና በአርአያም እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በክብር ሲገባ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው።
አስቀድሞም በነቢየ እግዚአብሔር ዘካርያስ እንደተነገረው “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ! እጅግ ደስ ይበልሽ፣ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ! እልል በይ! እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው! ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል… ሰላምን ይናገራል” (ትንቢተ ዘካርያስ ምዕራፍ ፱ ቁጥር ፱) በማለት እንደሚመጣና የሠላምንም ብሥራት እንደሚያበሥር ተናገሮ ነበር።
ሲመጣም “ሁሉም ፈጥነው ልብሳቸውን ወሰዱ፤ በሰገነቱም መሰላል እርከን ላይ ከእግሩ በታች አነጠፉት። ቀንደ መለከትም እየነፉ፣ – እዩ ነግሦአል አሉ” በማለት ሊደረግለት የሚገባውን ገልጿል (መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ፣ ምዕራፍ ፱፣ ቁጥር ፲፫)።
የሆሣዕና በዓል የቤተክርስቲያን ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ ሕዝቡ “ፀበርት” ወይም ዘንባባ በመያዝ “ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር – በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው” (መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፻፲፯ ቁጥር ፳፮) በማለት ስለተቀበሉት ይህን በማሰብና በማድረግ ቤተክርስቲያናችን ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ታድላለች።
በቤተክርስቲያን፣ በአራቱም ማዕዘናት ይህን በዓል የሚጠቅሱት የቅዱስ ማቴዎስ (ምዕራፍ ፳፩ ቁጥር ፩–፲፯)፤ የቅዱስ ማርቆስ (ምዕራፍ ፲፩ ቁጥር ፩–፲)፣ የቅዱስ ሉቃስ (ምዕራፍ ፲፱ ቁጥር ፳፱–፴፰) እና የቅዱስ ዮሐንስ (ምዕራፍ ፲፪ ቁጥር ፲፪–፲፭) ወንጌላት ይነበባሉ ።
በሆሣዕና ዕለት ከሌሎች እንስሳት ይልቅ ጌታን የመሸከም ክብር አግኝታ የተሸከመችው አህያ ናት። ጌታን የተሸከመችው አህያ ከዚያ በፊት ያላየችውና ያልተደረገላት ክብር ተደርጎላታል። አህያ ከዚህ በፊት ለኛ እህል ተሸክማ ስትሄድ ሂጂ እያልን በዱላ እንደበድባት ነበር፤ ነውም። ነገር ግን በሆሣዕና ዕለት እንኳን በዱላ ልትደበደብ ቀርቶ፣ ሰዎች በእርሷ ላይ ለተቀመጠው ጌታ ሲሉ ልብሳቸውን ሁሉ እያነጠፉላት በንጣፍ ላይ ተራምዳለች። ኢየሩሳለሌም ሲደርስ ከገጹ ብርሃን የተነሣ ከተማዋ ብርህት ሆነች፡፡
ሕዝቡ የሆነውን ሊያዩ ወጡ፡፡ ሕፃናት ፀሐይ ስትሰግድለት፣ መላእክት ከበው ሲያመሰግኑት አይተው በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የሰሌን ዝንጣፊ ይዘው “ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር” እያሉ አመስግነዋል፡፡ ሆሣዕና ማለት በልዕልና ጸንቶ የሚኖር መድኃኒት ማለት ነው፡፡
መልካም የሆሳዕና በዓል!!