ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– “የኮሮና ቫይረስ አሁናዊ ሁኔታን በተመለከተ” በመዲናይቱ የዳሰሳ ጥናት ማድረጉን የገለፀው አዲስ አበባ ጤና ቢሮ በአዲስ አበባ በግልና በመንግሥት ተቋማት 1 ሺ 302 የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ 30 የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸው እንዳለፈ በጥናት መረጋገጡን አስታውቋል።
“ኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከአፍሪካ 4ኛ መሆኗን እና የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም ከእለት እለት እየጨመረ ነው” ያሉት በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የጤና ትምህርት ባለሙያ አቶ ኤርሚያስ አድህና፣ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣው መመሪያ በተቋማት፣ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎችና በትምህርት ቤቶች በሚፈለገው ልክ እየተተገበረ አለመሆኑን አመልክተዋል።
“የጤና ባለሙያዎች ምቹ ባልሆነ ቦታ እና በቂ የህክምና ቁሣቁስ ባልተሟላበት መስራታቸው ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል” ሲሉ የተናገሩት የጤና ትምህርት ባለሙያ አቶ ኤርሚያስ፣ ለጤና ባለሙያዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሟላት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከከተማ አስተዳደር እንዲሁም ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።