– ሱዳን ወደድርድሩ መመለስን፣ ግብፅ በቀደመ ሴራዋ መቀጠልን መርጠዋል!
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአቡዳቢ ገዥ የሆኑት ልዑል አልጋ ወራሽ ሼኽ መሐመድ ቢን ዛይድ፣ ከቀናት በፊት በግብፅ ያደረጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ተከትሎ ግብፅና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከዚህ ቀደም ያሳዩ የነበረው ህብረት እየላላ መሆኑና ሁለቱ አገራት በተከታታይ የተናጠል አቋሞችን ማንፀባረቅ መጀመራቸው ተነገረ።
“ሙሐመድ ሙርሲን በኃይል አስወግዶ ወደ ስልጣን ለመጣው የአል ሲሲ አስተዳደር ዋነኛ የጉልበት ምንጭ ኤምሬትስ ነች። አልሲሲ እስላማዊ ወንድማማች ህብረትን በምትፃረረው አቡዳቢ ጎራ መቆማቸው ለስልጣን ቢያበቃቸውም ከአቡዳቢ የሚሰጡ የቢሊዮን ዶላርና የደህንነት እገዛዎችም ከባድ የሆኑ ደንቦችን እንዲያከብሩ ግዳጅ የሚጥሉ ናቸው። እነዚህን ግዴታዎች ‘አልሲሲ በአግባቡ አልተወጣም’ በማለት ኤምሬትስ 2016 ላይ ‘እኔ የATM ማሽን አይደለሁም’ ስትል የሰጠችው ማስጠንቀቂያም የሰሞኑን ጉብኝት ሚዛን ለመጠቆም አንደኛው ሊሆን ይችላል” በማለት የሚገልፀውና በአባይ ጉዳይ በየዕለቱ አዳዲስ መረጃዎችን በማውጣት የሚታወቀው ጋዜጠኛ እስሌማን ዓባይ ነው።
“ይህ የኤምሬትስ የበላይነት ተጠናክሮ ቀጥሎ የሰሞኑ የልዑሉ የካይሮ ጉብኝትም ከአዛዥና ታዛዥ ቆይታ የዘለለ እንደማይሆን በበርካታ አረባዊ ምሁራን እየተነገረ ይገኛል” ብሏል።
“መጋቢት ላይ ኢትዮጵያና ሱዳንን የማሸማገል ጥሪ ከአቡዳቢ ሲቀርብ ለግብጾች መርዶ መሆኑን የካይሮ ልሂቃን በርካታ የደህንነት መረጃዎች በአስረጂነት ጠቅሰው ሲገልፁት ነበር። በተለይም ኤምሬትስ ከእስራኤል ጋር ዕርቅ ማውረዷን ተከትሎ የእስራኤሉ ሞሳድ በሱዳን መንግስትና በናይል ውሃ አጠቃቀም ላይ ፈላጭ የሚሆንበት ጅምር መታየቱ እስራኤልና ኤምሬትስ ግብፅን ክፉኛ የሚጎዳውን የውሃ ካናል በደቡባዊ ቀይ ባህር ኤልያትና ሃይፋ መካከል ለመገንባት ስራ መጀመራቸው ተጠቅሰዋል።
ይባስ ብሎም ቢን ዛይድ ከሱዳን ጋር ለሳምንታት ከመከሩ በኋላ ወደ ካይሮ ያቀኑት የሱዳኑ ጦር መሪ አልቡርሃን ከግብፅ ጋር የፈጠሩትን ጥምረት ለመበጠስ ስለመሆኑ የደህንነት ምንጮችን ዋቢ ያደረጉ ትንተናዎች ጠቁመዋል” ያለው ጋዜጠኛ እስሌማን፣ አልሲሲ እና ቢንዛይድ ያደረጉት ምክክር በሁለታቸው መካከል ሌላ ባለስልጣን በሌለበት መሆኑም ለጉዳዩ ከባድነት ማጠናከሪያ እንደሚሆን አመልክቷል።
በተያያዘ፣ የግብፁ “ዲግኒቲ ፓርቲ” መሪ አህመድ ታንታዊ፣ የልዑሉን ጉብኝት ተከትሎ “ኤምሬትስ ለግብፅ ቁልፍ ስጋት በሆነው የግድቡ ጉዳይ ያሳየችው ግዴለሽነት ለካይሮ አደገኛ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ቤሊንግካት” የተሰኘው የስለላ ተቋም ሶስት ግብፃዊ ባለስልጣናትንና ዲፕሎማቶችን ዋቢ አድርጎ “ኤምሬትስ በትግራዩ ጦርነት ለኢትዮጵያ መከላከያ ድሮኖችን ከማቅረብ በተጨማሪ ኤርትራ ኢትዮጵያን እንድትደግፍም አድርጋለች” ብሏል።
ኤምሬትስ ከእስራኤል ጋር በመቀናጀት ለኢትዮጵያ ደህንነት ስትራቴጂክ የሆ ስራ መጀመሯና ሰሞነኛው የቢንዛይድ ጉብኝትም “ለአልሲሲ አድርግና አታድርግ የሚሉ ቀጫጭን ትዕዛዞች የተሞላ ስለመሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ኤምሬትስ ከግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ጋር የተያያዘው አለመግባባት መፍትሄ እንዳልሆነ አቋም በመያዝ መፍትሄው ለሶስቱም አገራት ድጋፍ የሚሆን እርዳታ ቢሆን ስለመሻሉም ለአልሲሲ አስረግጣለች ተብሏል።
በሌላ በኩል ሱዳን የካይሮን ወታደራዊ ነጋሪት ገሸሽ በማድረግ የግድቡን ጉዳይ ወደ አለማቀፍ ክስ ስለ መውሰድ በማሰብ ላይ መሆኗ ለኢትዮጵያ የጊዜ ፋታ ከመስጠቱ ባሻገር ይህ የካይሮ የመጨረሻ ካርታ አሁን ላይ በሱዳን ውድቅ መሆን ሌላው የአልሲሲ ኪሳራ መሆኑ እየተነገረ ሲሆን፣ አማራጭ ያለቀባት ግብፅ ወታደራዊ ድንገተኛ ጥቃት በተመረጡ የግድቡ ክፍሎች ላይ በማድረስ ሙሊቱን ማዘግየት የሚል ምክክር መጀመሯ ከውስጥ አዋቂ የወጡ መረጃዎችን ጠቅሰው ማዳ ማስርና ሌሎችም አውርተዋል።
“ይሁንና አለማቀፉ ማህበረሰብ ፍፁም ያጣጣለባት በመሆኑ ብቸኛው አማራጭ መደራደር ብቻ ነው” ያለው ማዳ ማስር፣ ግብጽ የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሳ ጥቃት ለማድድረስ ብትሞክር ወትሮም በውጭ ድጋፍ የቆመው የካይሮ ቤት አለማቀፍ ቀውስ እንደሚገጥመው አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ “ግብፅ የፍፃሜ ዕድሏን ቤንሻንጉል ላይ ያደረገች መስላለች” እየተባለ ሲሆን፣
ግብፃዊ የፖለቲካ ተንታኞች “ጉሙዞች ወደሱዳን ለመቀላቀል የሚያደርጉትን ትግል አረቦች ይደግፉ” ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውም የዚሁ የመጨረሻ ዕድል ሙከራ ማሳያ መሆኑ ተነግሯል።
ግብጻዊያን የፖለቲካ ተንታኞች እና አክቲቪስቶች “ኢትዮጵያን ለማደከምና ለማፍረስ ከአሁን የተሻለ ጊዜ የለም” በሚል የተቀናጀ ሥራ እየሰሩ መሆናቸውንና አረቦች እንዲያግዙም በግልጽ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
ከሰሞኑ ግብጻዊያን የፓለቲካ ተንታኝ እና አክቲቪስቶች በግልጽ በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እና ማህበራዊ ሚዲያዎች ብቅ እያሉ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመግባት የተለያዩ አገር አፍራሽ ሥራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን እየገለጹ ሲሆን በአገሪቱ ታዋቂ የሆነው የፓለቲካ ተንታኝ ከሰሞኑ በቴሌቪዥን ሥርጭት ላይ ቀርቦ “የቤንሻንጉል ክልል የሱዳን መሬት ስለሆነ ወደሱዳን ለማካለል የአረብ አገራት ድጋፍ እንዲያደርጉ” ሲል ጥሪ አቅርቧል።
“ቤንሻንጉሎች መሬቱ የኛ ስለሆነ ለቃችሁ ውጡ እያሉ የአማራ እና የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን እያባረሩ ነው። ግድቡ ያለው በዚሁ ክልል ስለሆነ ጉሙዞች እንደ ደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነፃ እንዲወጡ ማገዝ አለብን” ሲል ጥሪ ያቀረበው ይኸው ግብጻዊ “ይሄንን አጋጣሚ በመጠቀም የአብይ አህመድን መንግስት ማዳከም አለብን። ይህንን ማድረግ ካልቻልን ሌላ ተጨማሪ ዕድሎችን አናገኝም” ሲልም ተናግሯል።
በተመሳሳይ፣ ሼሪፍ ኤልሳሊይ የተባለ አክቲቪስት ከሰሞኑ በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች ያሉ የሽምቅ ተዋጊዎች የግብፅ መንግስት ድጋፍ እንዲሰጣቸው ጠይቆ “መንግስታችንም ይሄንን ተቀብሎ ወደስራ ገብቷል” ሲል ገልጿል።
ይሁንና፣ ቀደም ሲል ከግብፅ ጋር ተመሳሳይ አቋም ስታራምድ የቆየችው ሱዳን፣ ባልተጠበቀ መልኩ “ከታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ያሉ ልዩነቶች በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ይፈታሉ የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ” ማለቷ በሁለቱ አገራት መካከል በግድቡ ጉዳይ የነበረው ህብረት እየላላ መሆኑ ማሳያና መሆኑና ይህም ልዩነት የአቡዳቢው ልዑል ካይሮን ከጎበኙ በኋላ እየሰፋ መምጣቱ ተጠቁሟል።
“ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መሪ ቃል የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ፍላጎት አለኝ” ያለችው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ወሳኙን እና አዲስ ሃሳብና አሰራር የሚመጣበትን የአፍሪካ ህብረትን እንደሚያደንቅም ገልጿል።
ይህንኑ የሱዳን መንግስትን የተናጠል አቋም በሚመለከትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ”በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ላይ የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር አሁንም ቢሆን በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ጽኑ ፍላጎትት ነው” ሲሉ አመልክተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን አስመልክቶ በሱዳን በኩል ለቀረበው ሃሳብ፣ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ቢሮ ስብሰባ እንዲያካሂድ በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ-መንበር በኩል ጥሪ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ሀሳብ መጠየቋንና ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህ መሰረት በጉዳዩ ላይ ሲደረግ የነበሩ ድርድሮች ውጤት የተገኘባቸው መሆኑንም አምባሰደር ዲና ገልጸዋል፡፡