የህወሃት ቡድን ለወንጀል ተግባር ሊያውለው ይችል የነበረ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ መታገዱ...

የህወሃት ቡድን ለወንጀል ተግባር ሊያውለው ይችል የነበረ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ መታገዱ ተገለፀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጀነራል አቶ ዓለምአንተ አግደው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ የህወሃት ሕገ-ወጥ ቡድን ስድስት ቢሊየን 762 ሚሊየን 942 ሺህ 319 ብር ለወንጀል መፈጸሚያነት ማዋል እንዳይችልና በሕገ-ወጥ መንገድ እንዳያሸሽ መከላከል መቻሉን ገልፀዋል።

“ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕወሃት ሕገ-ወጥ ቡድን ታህሳስ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ ባከናወነው የሀብት ክትትልና ምርመራ ሥራ መጠኑ ብር 97,573,164.30 (ዘጠና ሰባት ሚሊየን አምስት መቶ ሰባ ሦስት ሺ አንድ መቶ ስልሳ አራት ብር ከሠላሳ ሳንቲም) የሆነ የሕወሃት ገንዘብ በሕግ አግባብ የውርስ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለሚመለከተው አካል አስተላልፏል” በማለት ዳይሬክቶሬት ጀነራሉ ተነግረዋል።

ሕገ-ወጥ ቡድኑ ሲቆጣጠራቸው በነበሩ፣ ገንዘብና ንብረታውን ለሕገ-ወጥ ዓላማው ሊጠቀምባቸው ይችላል በሚል በተጠረጠሩ ድርጅቶች እንዲሁም በጦርነት በተሳተፉ የጦር መኮንኖችና ሌሎች ባለስልጣናት ላይ በተደረገ የሃብት ክትትልና ምርመራ ውጤታማ ሥራዎች መሰራታቸውም ተመልክቷል።

“በዚህ መሠረት ከሕወሃት ጋር በመሰለፍ በጦርነት የተሳተፉ ዋና ዋና ተጠርጣሪዎች ገንዘብና ሃብት ላይ በተደረገ ክትትልና ማጣራት ሥራ ብር 54,237,565.36 (አምሳ አራት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሰላሳ ሰባት ሺ አምስት መቶ ስልሳ አምስት ብር ከሠላሳ ስድስት ሳንቲም) እንዲሁም ሌሎች ብዛት ያላቸው ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዲታገድ ተደርጓል” በማለት አቶ ዓለምአንተ አግደው አስታውቀዋል።

ከዚሁ ጋር በማያያዝም፣ በኤፈርት ሥር በሚተዳደሩ እና ተያያዥ የሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች ላይ በተከናወነ የሀብት ክትትልና ምርመራ ሥራ ብር 4,205,717,061.67 (አራት ቢሊዬን ሁለት መቶ አምስት ሚሊዮን ሰባት መቶ አስራ ሰባት ሺ ስልሳ አንድ ብር ከስልሳ ሰባት ሳንቲም) በፍ/ቤት ትዕዛዝ በማሳገድ እና ግምታቸዉ ከ 2 (ሁለት) ቢሊዬን ብር በላይ የሆኑ 179 የደረቅና የፈሳሽ ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ለማሸሽ ጥረት ሲያደርጉ የፍ/ቤት ትዕዛዝ በማውጣትና የጋራ የሕግ ትብብር ጥያቄ ለጅቡቲ መንግስት በማቅረብ ወደ አገር ማስመለስ መቻሉን የገለፁት አቶ ዓለምአንተ አግደው፣ በዚህም ህገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ የኤፈርት /ት.ዕ.ም.ዕ.ት ድርጅቶችን ገንዘብና ንብረት ለተጨማሪ የወንጀል ተግባር መፈጸሚያ እንዳያውል ከፍተኛ የመከላከል ሥራ መስራት ተችሏል በለዋል።

በአሁኑ ወቅት የወንጀልና የሃብት ምርመራው ተጠናቆ ፍ/ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የኤፈርት ድርጅቶች በፍ/ቤት በተሾሙ ገለልተኛ በባለ አደራ ቦርድ ስር ሆነው ለሕጋዊ አላማ ብቻ እንዲሰሩ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ፣ በተመሳሳይም በሕወሃት ሕገ-ወጥ ቡድንና በዚህ ቡድን ስር በነበሩ አመራሮች ቀጥተኛ ቁጥጥር ይደረግባቸዉ በነበሩና ቡድኑ የድርጅቶችን ገንዘብ ለወንጀል መፈጸሚያ ሊያዉል ይችል የነበሩ ሦስት ስቪል ማህበራት ላይ በተደረገ የሃብት ክትትልና ምርመራ ሥራ ብር 400,150,617.87 እና ሼር የተገዛበት ገንዘብ ብር 5,254,910.10 በድምሩ ብር 405,405,527.97 (አራት መቶ አምስት ሚሊየን አራት መቶ አምስት ሺ አምስት መቶ ሃያ ሰባት ብር ከዘጠና ሰባት ሳንቲም) በፍ/ቤት ትዕዛዝ በማሳገድ እና ገለልተኛ አስተዳዳሪ በፍ/ቤት በማሾም የማህበራቱ ገንዘብ በሕወሃት ቡድን ለሕገ-ወጥ ዓላማ እንዳይውል መከላከል መቻሉን አብራርተዋል።

አቶ ዓለምአንተ አግደው በበዚሁ መግለጫቸው ማጠቃለያም “ሕገ-ወጥ ቡድኑ ይቆጣጠራቸው የነበሩ ገንዘቦችና ሀብቶችን ለተጨማሪ ጥፋት እንዳይጠቀምና እንዳያሸሽ ቡድኑ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ማግስት ጀምሮ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ በፍጥነት በመሰራቱ የመከላከል ሥራውን ውጤታማ አድርጎታል። አሁንም ቀሪ ሥራዎችን ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮና ሌሎች ከሚመለከታው አካላት ጋር በጋራ በመሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል” ብለዋል።

LEAVE A REPLY