ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ሚያዚያ 19 ቀን 2013ዓ.ም ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት ገደማ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ነብር በሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ ተነግሯል።
በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ኮሚኒኬሽን ቢሮ እንዳስታወቀው፣ ነብሩ ባደረሰው ጥቃት ነዋሪነቷ አዘና 3ቱ ሰኞ ቀበሌ የሆነች አንዲት ሴት ከባድ ጉዳት ደርሶባት በግምጃ ቤት ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላት ሲሆን፣ ነዋሪነቱ አዘና ጉሲ የሆነ አንድ ግለሰብ ቀላል ጉዳት የደረሰበት መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
“ነብሩ በሁለቱ ግለሰቦች ላይ ጥቃት ካደረሰ በኋላ ወደ ገበያ ስፍራ በመውጣት ሌሎች ግለሰቦች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ሲል ከህብረተሰቡ በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ አልፏል” በማለትም የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።