ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ወደታላቁ የህዳሴ ግድብ “ዕቃዎችን እና የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን በማጓጓዝ ላይ የነበሩ 10 አሽከርካሪዎች በመተከል ዞን ማንጎ ከተማ ላይ በታጣቂዎች ተገደሉ” በሚል፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጭ የቆየው መረጃ ሐሰት መሆኑን የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።
የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሜጀር ጀነራል አስራት ዴኔሮ በሰጡት መግለጫ፣ እየተሰራጨ ያለው መረጃ ሐሰት መሆኑን ገልፀው “በትናንትናው ዕለት ከ70 በላይ አሽከርካሪዎች ወደ ህዳሴው ግድብ የተለያዩ እቃዎችን እና ማሽነሪዎችን ያለምንም ችግር አድርሰዋል” ብለዋል፡፡
“ታላቁ የህዳሴው ግድብ 24 ሰዓት ክትትል እና ጥበቃ የሚደረግለት ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ ከማንኛውም የደህንነት ስጋትም ነጻ ነው” ያሉት ሌተናል ጀነራል አስራት፣ “ወደ ካማሼ በመምጣት ላይ ያለ አንድ አይሱዙ በታጣቂዎች ተተኩሶበት ሹፌሩን ጨምሮ 3 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፤ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሀይል የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ሁኔታውን ተቆጣጥሮታል” ሲሉም ተናግረዋል።