የጆይ ኦቲዝም ማዕከል መስራቿ ወ/ሮ ዘሚ የኑስ በኮቪድ የህክምና ማዕከል ሆነው “ፀልዩልኝ”...

የጆይ ኦቲዝም ማዕከል መስራቿ ወ/ሮ ዘሚ የኑስ በኮቪድ የህክምና ማዕከል ሆነው “ፀልዩልኝ” አሉ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በኒያ ፋውንዴሽን ስር ጆይ የኦቲዝም ማዕከል የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት አቋቁመው ለበርካታ ወገኖች ደራሽ መሆን የቻሉት የጆይ ኦቲዝም ማዕከል መስራችና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ዘሚ የኑስ፣ በኮቪድ 19 ቫይረስ ተይዘው ፅኑ ህሙማን ማዕከል ሆነው ለመላው ኢትዮጵያውያን “በፀሎት አስቡኝ” የሚል መልዕክት አስተላለፉ።

ወንድ ልጃቸው የአዕምሮ እድገት ዝግመት ያለበት ሆኖ መወለዱ ስለችግሩ በጥልቀት እንዲረዱና ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች መሰሎችም መፍትሔ ለማስገኘት ብዙ ሲደክሙ እነደነበር ይታወቃል።

የኦቲዝም ታማሚ ልጃቸውን ለማሳደግ የተጋፈጡትን ከባድ ሕይወት በአደባባይ በመናገርና ለዘመናት ከህመሙ ጋር ተያይዞ የነበረውን አጉል እምነትና ዝምታ በመስበር ለብዙ ወገኖች ደራሽ የሆኑት ፋና ወጊዋ ወ/ሮ ዘሚ የኑስ፣ አሁን በመተንፈሻ መሳሪያ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛሉ።

ኮቪድ 19 ቫይረስ ለሀገራቸው ብዙ መልካም ነገር ያደረጉ እና ገና ብዙ የሚሰሩ በሕዝብ ዘንድ የሚወደዱ  ባለውለታዎች በሞት እያሳጣ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ የወ/ሮ ዘሚ የኑስ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ መገኘት ህብረተሰባችን የጉዳዩን አሳሳቢነት ትኩረት እንዲሰጠውና ራሱን እንዲጠብቅ የሚያነቃ አስደንጋጭ መልዕክት መሆኑም እየተነገረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ነገ ዝግጅት ክፍልም መላው ህብረተሰባችን ራሱንና ቤተሰቡን ከዚህ ገዳይ ቫይረስ እንዲጠብቅ እያሳሰበ፣ ለአገር ባለውለታዋ ወ/ሮ ዘሚ የኑስ ምህረቱን እንዲልክ ከልብ ይመኛል።

LEAVE A REPLY