ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ሰሞኑን “የመከላከያ ሠራዊቱን የደንብ ልብስ ለብሰው ሰዎች ላይ ጉዳት አደረሱ እና በሐይማኖታዊ ቦታ ተገኙ” የተባሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በሚመለከት መከላከያ መግለጫ ሰጠ።
የመከላከያ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ “የመከላከያ ሠራዊት አባላትና አመራሮች በስራና ከስራ ውጪ በሚሆኑባቸው ጊዜያት የደንብ ልብስ ለብሰው መገኘት የሚችሉባቸው ቦታዎችና ጊዜዎችን የሚደነግጉ መመሪያዎችና ደንቦች እንዳሉ ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሶ በሐይማኖታዊ ቦታዎች፣ በመጠጥ ቤቶች፣ በፖለቲካዊ ፕሮግራሞችና ባልተፈቀዱ በሌሎች አካባቢዎች ላይ መገኘት አይቻልም” ሲሉ ተናግረዋል።
“ባልተፈቀዱ ቦታዎችና ሁኔታዎች የሠራዊቱን የደንብ ልብስ ለብሶ መገኘት እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ያስቀጣል” ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፣ በዚሁ መግለጫቸው “ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ በተላለፈ ተንቀሳቃሽ ምስል የመከላከያ ሠራዊቱን ዩኒፎርም በመልበስና በተሽከርካሪ በመንቀሳቀስ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላት ላይ የሰራዊቱ አባላት መሆን አለመሆናቸውን በማጣራት በወታደራዊ ቅጣትና በሲቪል ሕግ ለመጠየቅ ምርመራ ተጀመሯል” ሲሉ አስታውቀዋል።
ሕብረተሰቡ እንዲህ አይነት ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት ለሚመለከተው አካል በመጠቆም ከደንብና መመሪያ ውጪ የሆኑ ድርጊቶችን መከላከል እንደሚገባው የጠቆሙት የመከላከያ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ “በሠራዊቱ ስም ሕገ ወጥ ተግባራትን የሚያከናውኑትን ማጋለጥ ይገባል” በማለትም አሳስበዋል።