ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የጸሎተ ሀሙስ በአል፣ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተገኙበት ዛሬ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በልዩ ስነ ስርአት ሲከበር ውሏል።
በዚህ እለት የሚፈጸመው የፍቅርና የትህትና ምልክት የሆነው “የሕጽበተ እግር” ሥነ-ስርአትም በቤተክርስቲያኒቷ አባቶች አማካኝነትና ቤተክርስቲያኒቱ ስርአት መሰረት በተለያዩ አድባራት ተከናውኗል።
የጸሎተ ሐሙስ በአልን በማስመልከት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በሰጡት ቃለ ቡራኬ “ይህ በአል የፍቅርና የትህትና እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ወገን እርስ በርስ ሊፋቀርና ሊከባበር ይገባዋል። እንደ አገርም ሠላማችንን ፍቅራችንን እና አንድነታችንን ጠብቀን ልንኖር ይገባል። ይህንን ማድረግ ከተሳነን የእግዚአብሔር በረከት ስለሚርቅ ለአገርም ለህዝብም መልካም አይሆንም” ብለዋል።
በጸሎተ ሐሙስ እለት በቤተ ክርስቲያኒቱ ስርአት መሰረት ስግደት፣ ጸሎት፣ የቅዱሳን መጻህፍት ምንባባት፣ ሕጽበት እግር እና ቅዳሴ ይከናወናል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሥርዓት መሰረት በጸሎተ ሐሙስ ቀን ከካሕናት ትልቁ ታናናሾቹን ያጥባል፡፡ ሊቀ ጳጳሱም ካሉ ሊቀ ጳጳሱ ተንበርክከው የአገልጋዮችን እግር ያጥባሉ፡፡ ኢየሱስ የፈፀመውን ሁሉ ይፈፅማሉ፡፡ ትሕትና ሰርቷልና ትሕትናውን ይሠራሉ፡፡
ካሕናቱ እግራቸውን የሚታጠቡት በለመለመ ቅጠል ሲሆን ይህም የልምላሜው ዘመን፤ መልካሙ ዘመን መድረሱን የሚያመላክት ነው፡፡
በጸሎተ ሐሙስ የነበረው መታጠብም ከሐጥያት የመንጻት ዘመን መድረሱን የሚያመላክት ነበር፡፡
ከሰሞነ ሕማማት ቀን መካከል አንዷ የሆነችው ሐሙስ የተለያየ ስያሜ ይሰጣታል፡፡ ፀሎት የተደረሰባት ነበርና “ፀሎተ ሐሙስ” ትባላለች፡፡
ዝቅ ብሎ የሐዋርያትን እግር አጥቧልና ይህም ኢየሱስ የዓለምን ሐይጢያት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ያሳያልና ቀኗም “ሕፅበተ ሐሙስ” ትባላለች፡፡ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቍርባን በዚህ ቀን ተመሥርቷልና ዕለቱ “የምሥጢር ቀን”ም ተብሎ የጠራል፡፡ ይኸውም ጌታ ኅብስቱንና ጽዋውን አንሥቶ “ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል ላይ የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ” በማለቱ ነው፡፡
“ክርስቶስ መሥዋዕተ ኦሪት መቅረቱን አሳዬ፤ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመኾኑ ይህ ዕለት ‘የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ’ ይባላል” ይላሉ ሊቃውንት፡፡ ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታ ለአዳምና ለልጆቹ ዅሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለኾነ ሐሙስ “የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ” ተባለ ይላሉ፡፡
ሊቃውንተ ቤተክርስያን፣ ዕለቷ ለኃይጢያትና ለዲያብሎስ ባሪያ ኾኖ መኖር ማብቃቱ የተገለጠበት፤ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለ ኾነ “የነጻነት ሐሙስ” ይባላልም ብለዋል፡፡
የበረቱ ክርስቲያኖች ከጸሎተ ሐሙስ በኋላ እስከ ትንሣኤ ድረስ አይበሉም፡፡ ይህም፣ ኢየሱስ ለሰው ዋጋ ሰጥቶ ከሰማየ ሰማያት እንደወረደ ሁሉ የሰው ልጅ አምላኩ ዋጋ ለሰጠው ፍጡር ዋጋ መስጠት ስላለበት ነው፡፡
ፈጣሪ ያከበረውን ፍጡር አክብር፤ ትሕትናን ከእርሱ ተማር፤ በብርሃን ውስጥ ዓይንህን ካጨለምክ ጨለማ ይመጣብሃል፤ ብርሃን ይርቅሃል፤ በጎ ነገር በበዛባት ዓለም ውስጥም ክፉን ከመረጥክ መከራው ይመጣብሃል፡፡ በጎውን ምረጥ ትሑት ሁን ያን ጊዜ ያሰብከው ይሳካል፡፡
ከሰሞነ ሕማማት በኋላ በሚመጣው የትንሣዔ ብርሃንም ያላቸው የሌላቸውን በማየት፣ የታመሙትን በመጠየቅ፣ እስረኞችን በመጎብኘት እና ለተፈናቀሉ ወገኖችን አብሮነትን በማሳየት ማክበር ክርስቲያናዊ ተግባር በመሆኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ይህን እንዲያደርጉ ኢትዮጵያ ነገ ጥሪዋን ታቀርባለች።
መልካም “የጸሎተ ሐሙስ” በዓል!