ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም. በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት አካላት፣ የሲቪል ማኅበራት እና የሚዲያ ተቋማት “ሊያከብሯቸው፣ ሊፈጽሟችው እና ሊያስፈጽሟቸው ይገባል” ያላቸውን ባለ 6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ ይፋ አደረገ።
በአጀንዳው ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ባለድርሻ አካላት የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅን በተመለከተ የሚወስዱትን ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲያሳውቁ፣ ለሰብአዊ መብቶች በቁርጠኝነት እንዲቆሙ፣ ለሥርዓተ-ጾታ ምላሽ ሰጪ የሆነ የምርጫ ሂደት እንዲኖር ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ፣ ለሰብአዊ መብት መሻሻል የሚያግዙ የሕግና ፖሊሲዎች ማሻሻያ ቃል ኪዳን እንዲገቡ፣ የመንቀሳቀስ፣ የመደራጀት፣ መረጃ የማግኘትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲረጋገጥ እና ከግጭት ቀስቃሽ፣ የጥላቻ ንግግር እንዲሁም ከኃይል እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ እንዲቆጠቡ፤ ለዚህም በይፋ ቃል እንዲገቡና እና በገቡት ቃል መሰረት እንዲተገብሩ ጥሪውን አቅርቧል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ በሀገራዊ ምርጫው አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት በኮሚሽኑ የተቀመጡትን የሰብአዊ መብት አጀንዳ ነጥቦች አትኩሮት ሰጥተው እንዲመለከቷቸው፣ ቃል እንዲገቡ በጠየቅናቸው ጉዳዮች ላይ የሚገቡትን ቃልኪዳን እንዲያሳውቁ እና በአጀንዳው በተቀመጠው መሰረት ሰብአዊ መብቶችን በማክበር እንዲቀሳቀሱ” ጥሪ አቅርበዋል።