ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን፣ በአዲስ አበባ ከባእድ ነገሮች ጋር ተቀላቅሎ ለገበያ ሊቀርብ የነበረ ከ3 ሺህ 300 ኪሎ ግራም በላይ ቅቤ፣ 480 ኩንታል በርበሬ፣ 1 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ለቂቤ መከለሻ የሚውል የአትክልት ቅቤና የፓልም ዘይት እንዲሁም 6 መቶ ኪሎ ግራም ማር በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
“በአራት ክፍለ ከተሞች ባካሄድነው ክትትል በዚህ ህገወጥ ድርጊት ላይ በተሳተፉ 24 ድርጅቶች ላይ እርምጃ በመውሰድ ተሳታፊ ግለሰቦችም በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል” ያለው የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን፣ በቁጥጥሩ ወቅት ቅቤን ለመከለስ አገልግሎት የሚውሉ የአትክልት ቅቤ፤ ፓልም ዘይት እንዲሁም በርበሬ ለመከለስ የሚሆን ከደረጃ በታች የሆነ ለሰው ምግብነት የማይውል የበርበሬ ተረፈ ምርት፤ የሻገተ በርበሬ መገኘቱንም ገልጿል።
ቤቶቹ ለምግብ ማምረት ስራ ፍቃድ የሌላቸው እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የንፅህና ጉድለት ያለባቸው መሆኑን ያመለከተው ባለስልጣኑ፣ ህብረተሰቡ በበዓላት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስቦ “አጠራጣሪ ነገር ሲገጥም በነፃ የስልክ መስመር 8482 በመደወል ጥቆማ ማድረስ ይቻላል” ብሏል።