ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከሚያዝያ 11-16 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መስተዳደር ስር በሚገኙ አንዳንድ የምርጫ ክልሎችና በርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ያደረገው የመስክ ምልከታ ሪፖርት አውጥቷል።
ተቋሙ በመስክ ክትትልና ምልከታ ወቅት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ዲሞክራስያዊ እና ተአማኒ ምርጫ ለማድረግ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ በሚል “ለየኋቸው” ካላቸው ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ በአገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ወይም የእውቅና ፈቃድ በተሰጣቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሰጠ በቂ የስነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት አለመኖሩ አንዱ መሆኑን አስታውቋል።
“የመራጩን ህዝብ የትምህርት ደረጃና ተዛማጅ ጉዳዮችን ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ የስነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች ለሚገኙ መራጮች የሚሰጥበት ሁኔታ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ሲልም የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋሙ አመልክቷል፡፡