የስቅለት በዓል እየተከበረ ነው!

የስቅለት በዓል እየተከበረ ነው!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅን ለማዳን ሲል የተቀበላቸው መከራዎች የሚታወሱበት የስቅለት በዓል፣ በመላ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ እንደየቤተ እምነቱ በልዩ ልዩ ሀይማኖታዊ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡

በዓሉ በክርስትና እምነት ተከታዮች፣ ማለትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን በስግድት እና በልዩ ልዩ ጸሎት፣ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትም በተለያዩ የወንጌል ስነ-ስርዓቶች ዛሬ አርብ እየተከበረ ሲሆን፣ የትንሣኤ በዓል ሲከበር በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ መሆን እንዳለበትም የሃይማኖት መሪዎች አሳሰበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ የትንሣኤ በዓልን አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት “ከገባንበት የጨለማ ጉዞ መዉጫዉ የአምላክን አብነት መከተል ነው። አሁን በኢትዮጵያ የሚታየውን የሰላም እጦት ለመሻገር በአንድነትና በጋራ ተወያይቶ ችግሮችን ለመፍታት የተከናወነው ተግባር እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ያመጣው በመሆኑ ዕርቅና ይቅርታ ላይ ሊሠራ ይገባል” ብለዋል፡፡

“የሐሳብ ልዩነትን በኃይል ለመፍታት መሞከር ጥላቻን መዝራት ነዉና ለሰላም እርስ በርስ መጠባበቅና መደማመጥ ተገቢ ነው” ያሉት የሃይማኖት አባቶቹ፣ ምዕመናን በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጾምና ጸሎታቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

“እለተ አርብ (ስቅለት) የማስተሰረያ ቀን!”

“ማስተሰረይ” እግዚአብሔር ለኃጢአተኛ ሰው ይቅርታን እንዲያገኝና ከራሱ ጋር እንዲታረቅ የሠራው ሥራ ነው። በብሉይ ኪዳን የቃሉ ትርጉም “ማጥፋት”፣ “መሸፈን”፣ “ማስወገድ” ወይም “መጥረግ” ማለት ነው።
ኃጢአተኛው በሚያቀርበው መሥዋዕት ከእግዚአብሔር ይቅርታን ለመግዛት አይሞከርም። ይልቁንም እግዚአብሔር ለኃጢአተኛው፣ በጸጋው ከእርሱ ጋር ሊታረቅ የሚችልበትን መንገድ ሰጠው። የእርቅ መሠረታዊ ሃሳብ፣ በሌላ እንስሳ መሠዋት እግዚአብሔር የኃጢአተኛው ኃጢአት እንዲሸፈን ያደርግ ነበር።

በብሉይ ኪዳን ዘመን፣ የሰው ልጅ በኃጢአቱ ምክንያት የመጣበት መከራ እና ችግር በጣም አስጨናቂ ነበር።  ኃጢአቱንም ለማስተስረይ (ለማስደምሰስ፣ ይቅር ለማስባል፣ ለማሳጠብ) ከአሮን ወገን (ቤተሰብ) የሆኑት ሊቀ ካህናት በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን የተቀደሰውን በፍታ ለብሶ፣ ሁለት አውራ ፍየሎችን ይወስዳል፤ አንደኛውን ለኃጢያት መሥዋዕት ያደርገዋል፣ ደሙን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ያመጣዋል፣ በቃል ኪዳኑ ታቦትም ይረጨዋል።

ማንም ወደ ውስጠኛው መቅደስ ሊገባ የሚችለው በዚህ ጊዜ ብቻ ነው (ዕብ. 9፥6-7)። በሁለተኛው አውራ ፍየል ላይ ሊቀ ካህኑ እጁን ይጭንበትና የሕዝቡን ኃጢያት ይናዘዛል። ከዛም ፍየሉ ወደ ምድረ በዳ ይለቀቃል። እነዚህ ሁለት ድርጊቶች ሁለት የማስተስረያ ድርጊቶች ያቀፉ ናቸው። ወደ ቅድስተ ላዕለ-ማዕከሉ መቅረብ፣ የኪዳኑ ታቦቱ መክደኛ፣ ወደ ቅዱሱ አምላክ ለመምጣት ደም መፍሰስ እንዳለበት፣ ለሕዝቡ ማስታወሻ ነው። ሁለተኛው ፍየል የሚወሰደው ወደ ተቃራኒው ወደ ምድረ በዳ አቅጣጫ ነበር። አንዱ ወደ ቅዱሱ አምላክ የሚወስደን፤ ሌላኛው ደግሞ፣ የሕዝቡን ኃጢያት ወደ ባዶ ስፍራ ይወስድላቸዋል።

በአጭሩ አጠቃላይ ድርጊቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ በማስተስረያ ቀን በአመት አንዴ ሁለት ፍየሎችን ይዘው ይቀርባሉ፤ የመጀመሪያውን ፍየል አርደው ደሙን በማስተስረያው መክደኛ ላይ ከጊደሩ ደም ጋር ሲረጩት አንደኛው ፍየል ላይ ግን ሁለት እጃቸውን ጭነው የህዝቡን ኃጢአት ያሸክሙት እና በተመረጠው ሰው አማካኝነት ወደ ዱር (በረሃ) እንዲኮበልል ይደረግ ነበር፡፡

የመጀመሪያው ፍየል መታረዱ እስራኤላውያን የኃጢአት ቅጣት ሞት እንደሆነ እንዲረዱ ሲሆን የሁለተኛው ፍየል ኃጢአታቸውን ተሸክሞ ወደ ዱር እንዲሸሽ መደረጉ ደግሞ ኃጢያታቸውን የሚሸከመው ኃጢአቱን ከነ እርሱምን ያክል እንደሚያርቀው እንዲረዱ ነበር ይህም ለሐዲስ ኪዳን ጥላ መርገፍ
ምሳሌ ነበር፡፡
(ዘሌ. 10፡12-17፤ ዘሌ.16፡23-34፤ ዘሌ. 16፡32)

መድኃኒታችን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ፍየሎቹ፣ እና እንደ ሊቀካህናቱ፣ ሊቀ ካህናት፣ መሥዋዕት አቅራቢ፣ አስታራቂ  መሥዋዕት ሆኖ መስቀሉን መሰዊያ አድርጎ መሥዋዕቱን ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ተቀብሎ ኃጢአታችንን ተሸክሞ ኃጢአታችንን ከኛ ለማራቁ እና ስለ ኃጢአታችን መሞቱን የሚያመላክት ነበር፡፡ ይህች “እለተ አርብ የማስተስረያ ቀን” በክርስቶስ ኢየሱስ መሥዋዕትነት ለዳንን ክርስቲያኖች ልዮ ቀን ነች። አንድ ጊዜ መሥዋዕት፣ አስታራቂ ካህን፣ መሥዋዕት ተቀባይ ታራቂ ሆኖ ሞት ሊይዘው የማይችል ዘላለማዊ ጌታ በኩረ ትንሳኤ ነውና ለዘለዓለም የማይደገም፣ የማይሻሻል፣ ሌላ መሥዋዕት የማይሻ አድርጎ ራሱን አቅርቦ በአባቱ ቀኝ ተቀምጧል ክብር ከቸር አባቱ ከአብ ጋር ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለታረደው በግ ይሁን አሜን!

መልካም የስቅለት በዓል!

LEAVE A REPLY