ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከምዕራብ ጎጃም ቡሬ ወደ ነቀምት በሚወስደው መንገድ ሰዎችን ይዞ ይጓጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ‘አምሮ’ የተባለ ወረዳ ላይ ሲደርስ በታጣቂዎች በደረሰበት ጥቃት 15 ንፁሃን ዜጎች መገደላቸው ተገለፀ።
“ከቡሬ ጎጃም ወደ ነቀምት አንድ መኪና ህዝብ ጭኖ በመሄድ ላይ እያለ የአባይ ወንዝን እንደተሻገረ የሆነ ዳገት ይዞ ልክ ወደ 10 ኪ.ሜ ወደ እኛ ወረዳ ሳይገባ ነው ክስተቱ የተፈፀመው” በማለት የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ብርሃኑ ይባሰን ተናገረዋል።
ሰላማዊ ህዝብ ጭኖ የሚሄድን መኪና አስቁመው ነው ይህን እርምጃ የወሰዱት፤ መኪናውን ካስቆሙ በኋላ ህዝቡን በማውረድ መኪናውን ወደ ቡሬ ጎጃም ወደአባይ በረሃ በመመልስ ነው ግድያውን የፈፀሙት” ሲሉ ገልፀዋል።
የሟቾች ቁጥር 15 እንደሚደርስ እና የቆሰሉት እንዳልተለዩ አያይዘው የገለፁት ኮማንደር ብርሃኑ ይባሰን “ከሞቱት 15ቱ ውስጥ የኦሮሞ እና የአማራ ብሄር ተወላጆች እንዳሉበትና ሰው በማይደርስበት ቦታ የግፍ አገዳደል እንደተፈጸመባቸው ጠቅሰዋል።
ይህን ድርጊት የፈፀመው ኦነግ ሸኔ ነው በማለትም የድርጊቱን ፈፃሚዎች አስታውቀዋል።