ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሱዳን ታጣቂዎች ትናንት በምዕራብ ጎንደር ዞን መንዶካ ልዩ ስሙ እንዲብሎ በተባለ ቦታ፣ ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ እስከ ጠዋት 4 ሰዓት ተኩስ ከፍተው የግብርና ባለሀብቶችን ካምፕ ማቃጠላቸው ተነግሯል።
ከሱዳን ድንበር በ70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው በምትገኘው መንዶካ የሱዳን ኃይሎች ከርቀት ከፍተኛ ድምፅ ያለው መሳሪያ ሲተኩሱ እንደነበር፣ በአንፃሩም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት መደበኛ ወታደሮችና ፀረ ሽምቅ ተዋጊዎች፣ የአካባቢ ሚሊሺያና ሌሎችም የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የአፀፋ እርምጃ የሱዳን ኃይሎች ወደመጡበት መመለሳቸውን በዚህም አካባቢው ሊረጋጋ መቻሉን የአካባቢውን ነዋሪዎች ዋቢ ያደረጉ ዘገባዎች አመልክተዋል።
ከያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ በአንዳንድ የምዕራብ አማራ ወረዳዎች ዘልቀው በመግባት የባለሀብቶችን ንብረት የሚያወድሙት የሚዘርፉትና የሚያቃጥሉት የሱዳን ታጣቂዎች አሁንም ድረስ ከኢትዮጵያ ግዛት እንዳልወጡ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ማስታወቁን ይታወሳል።