ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በስድስት የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ መደቦች አዳዲስ ተሿሚዎችን መሰየማቸው ታውቋል።
የሹም ሽሩ ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ አጣዬና አከባቢው ከተከሰተው አሰቃቂ ግድያና ውድመት ጋር ስለመያያዙ በይፋ የተገለፀ ነገር የለም። በግጭቱ ከ250ሺ ሰዎች በላይ የተፈናቀሉ ሲሆን ከተሞችም ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መውደማቸው የተዘገበ ሲሆን እሰካሁን ሀላፊነቱን የወሰደ አካል አለመኖሩ ተመልክቷል።
ገዢው ፓርቲ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ አልቻለም በሚል የሚከሰስ ሲሆን የክልሉ መስተዳደር የሕዝቡን ቁጣ ለማርገብ ሰሞኑን ግምገማ ላይ እንደነበር ይታወቃል።
ይህነን ተከትሎ አቶ ተሻገር አገኘሁ አዳዲስ ተሿሚዎችን ይፋ ያደረጉ ሲሆን በዚህም መሰረት ፡ –
1. አቶ ሰማ ጥሩነህ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኀላፊና የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ
2. ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፤
3. ኮሎነል ባምላኩ አባይ በቢሮ ኀላፊ ደረጃ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፤
4. አቶ ዝጋለ ገበየሁ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ
5. አቶ ሀብታሙ ሞገስ የአማራ ክልል ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር፤
6. አቶ ሙሉጌታ አበራ የአማራ ክልል የፍትሕ ማሰልጠኛና የሕግ ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር፤ ሆነው ተሹመዋል፡፡