ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዚያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ህወሓት እና ሸኔ በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ያስተላለፈው የውሳኔ ሃሳብ የቀረበለት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት፣ ድርጅቶቹ “ሽብርተኛ” መባላቸውን ለመቃወም የሚያስችል ማስረጃ ካላቸው ለምክር ቤቱ እንዲያቀርቡ የጥሪ ማስታወቂያ ማውጣቱ ታውቋል።
የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 2ዐ ንኡስ አንቀጽ 2 መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበውን ሃሳብ የተመለከተው ም/ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ነው ጥሪውን በማስታወቂያ የገለፀው።
“በአዋጁ አንቀጽ 21 ንኡስ አንቀጽ 1 በተደነገገው መሠረት ሁለቱ ድርጅቶች የውሳኔ ሀሳቡን ለመቃወም የሚያስችል ማንኛውም ዓይነት ማስረጃ ካላቸው ይህ ማስታወቂያ በመገናኛ ብዙሃን ከተነገረበት ሰዓት ጀምሮ ባሉት 48 ሰዓታት ውስጥ በምክር ቤቱ ጽ/ቤት በአካል በመገኘት ማቅረብ ይችላሉ” ሲል አስታውቋል።