መከላከያ እዩ ጩፋን ሊከሰው መሆኑን አስታወቀ!

መከላከያ እዩ ጩፋን ሊከሰው መሆኑን አስታወቀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና“እዩ ጩፋ የተባለ ግለሰብ በቅርቡ በሐይማኖት ስም እየተከተሉኝ ነው ያላቸውን ወታደሮች  ክብር ባልጠበቀ መልኩ ከነ ዩኒፎርማቸው በቪዲዮና ፎቶ ቀርፆ በአደባባይ እንዲሰራጭ አድርጓል።

ይህ ድርጊትም የሰራዊቱን ስም እንዲሁም ታማኝነት በማሳጣት ለግል ፍላጎት እና ጥቅም ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የተፈፀመ ድርጊት በመሆኑ መከላከያ በህግ ለመጠየቅ ተዘጋጅቷል” ሲሉ የሰራዊቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ አስታውቀዋል።

ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፣ የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት እዩ ጩፋ ላይ ክስ ሊመሰርት መሆኑን አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ግለሰቡ የሰራዊቱን አባላት ክብር ባልጠበቀ መልኩ በሐይማኖት ስም ከነዩኒፎርማቸው እንደሆኑ የፈፀመውን ድርጊት በቪዲዮና ፎቶ ቀርፆ በአደባባይ እንዲሰራጭ ማድረጉ ወንጀል መሆኑን አመልክተው “ጥቂት የሰራዊታችን አባላትም ይህን ፍላጎት ለማሟላት የሁሉም ኢትዮጵያውያን መለያ የሆነውን ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሰው ተሳታፊ የሆኑ እንደነበሩ ተረጋግጧል፤ ተሳታፊዎቹም በመከላከያ ወታደራዊ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ተይዘውና ታስረው ጉዳያቸውን ወደ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የማጣራት ስራ እየተሰራ ይገኛል” ብለዋል።

በዚህ አይነት ጥፋት ከዚህ ቀደምም በተለያዩ የእምነት ተቋማት የተገኙ አባላት ላይ የእርምት እርምጃ ተወስዶ እንደነበረ ያስታወሱት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ “ከዚህ በኋላም የእምነት ተቋማትና መላው ህዝብ የመከላከያ ሰራዊቱን ዩኒፎርም ለብሶ በእምነት ተቋማት፣ በህዝቡ ዘንድ  ነውር በተባሉ የመጠጥ፣ የሱስ፣ የቁማር ወዘተ ቦታዎች የሰራዊት አባል ሆነ አስመሳይ ዩኒፎርም ለባሽ ሲመለከት እንዲጠቁም” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሎኔል ጌትነት አዳነ መግለጫቸውን ሲያጠቃልሉም “ሰራዊታችን፣ በጋብቻና በቀብር ጊዜ፣ በእምነት ቦታዎች ክብሩን በጠበቀ መልኩ የሚከወኑ ስርዓቶች መኖራቸውና ሰራዊቱም እምነት ካለው ከህዝብ የወጣ በመሆኑ በየግሉ ሐይማኖት ያለው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በኛ በኩል በህጋችን የተፈቀዱና የተከለከሉ ጉዳዮችን በውስጣችን የማስረፅ ስራ ይሰራል” ሲሉ ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY