ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ነዋሪ የሆኑ አምስት ሰዎች ለትንሳኤ በዓል ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ በ35,000 ብር የገዙት የቅርጫ በሬ ራሱን አጥፍቶ መገኘቱ የተነገረ ሲሆን፣ የበዓሉ ዕለት ደግሞ አንድ የከተማዋ ነዋሪ የጎረሰው ጥሬ ስጋ አንቆት ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ አስታውቋል።
አምስቱ ሰዎች እያንዳንዳቸው 7,000 ብር አዋጥተው በ35 ሺህ ብር የገዙት በሬ፣ አንድ ግቢ ውስጥ በሚገኝ የዛፍ ግንድ ላይ ታስሮ ሳለ የታሰረበትን ገመድ በጥሶ ለማምለት ባደረገው ትግል ታንቆ መሞቱና ባለቅርጫዎቹም ቅርጫ ስጋቸውን ለመከፋፈል ዘንቢላቸውን ይዘው በጠዋት ቦታው ላይ ሲደርሱ በገጠማቸው ነገር ክፉኛ መደንገጣቸው ነው የተነገረው።
እንደዚሁም፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ቦታው “ካዲስኮ” አካባቢ ነዋሪ የሆነ አንድ የ30 ዓመት ግለሰብ ከጓደኛው ጋር በመሆን ቤት ውስጥ ጥሬ ስጋ ሲበላ አንቆት ሕይወቱ ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።