ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሙዚቃ ሸክላ በማሳተም፣ የምሽት ክበብ በመክፈትና ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ባንድን ወደውጭ ይዞ በመጓዝ፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ አጀማመር ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረጉት “ፋና ወጊው” ባለሙያ አቶ አምኃ እሸቴ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ከ1941 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለማሳደግና አለም አቀፋዊ ተደማጭ ለማድረግ ሲታትሩ እንደኖሩ የሚነገርላቸው አቶ አመኃ እሸቴ “አመኃ ሪከርድስ” በተሰኘ የሙዚቃ አሳታሚያቸው ከ103 በላይ ነጠላ ሙዚቃዎችንና ለቁጥር የሚያታክቱ የሸክላና ካሴት አልበሞችን ያሳተሙ ሲሆን ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ባንድ ወደ አሜሪካን ይዞ በመጓዝም “ነጋሪት” ክለብን ከፍተው ነበር።
በኢትዮጵያ ከቀደምቶቹ ሙዚቃ ቤቶች አንዱ የነበረው የ”ሐራምቤ ሙዚቃ ቤት” ባለቤት የነበሩት አቶ አመኃ፣ ጥላሁን ገሠሠን፣ መሐሙድ አሕመድንና አለማየሁ እሸቴን ጨምሮ ለብዙ ሙዚቀኞችና ድምፃውያን ሰፊ ዕድል የከፈቱ ታላቅ የአገር ባለውለታ ነበሩ።
ዛሬ ከቤተሰቦቻቸው ባገኘነው መሰረት የታላቁ የአገር ባለውለታ አመኃ እሸቴ የቀብር ሥነ ሥርአት ነገ ማክሰኞ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በ9:00 የሚፈፀም ይሆናል።
የኢትዮጵያ ነገ ዝግጅት ክፍል፣ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ አጀማመር ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ባደረጉት “ፋና ወጊው” ባለሙያ አቶ አምኃ እሸቴ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው መጽናናትን ይመኛል።