ከቀናት በፊት ከኃላፊነታቸው የተነሱት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በሞት ተለዩ!

ከቀናት በፊት ከኃላፊነታቸው የተነሱት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በሞት ተለዩ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ከአማራ ክልል የፀጥታ ሁኔታ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ከቀናት በፊት ከኃላፊነታቸው የተነሱት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ መሞታቸው ታውቋል።

አቶ አበረ አዳሙ ከሀላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ ላለፉት ጥቂት ቀናት፣ በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆች “ሰኔ 15ትን ጨምሮ የተለያዩ ሚስጥራዊ ጉዳዮችን ለአለም አቀፍ ሚዲያ ይፋ አደርጋለሁ!” ብለዋል የሚሉ መረጃዎች ሲሰራጩ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ እስካሁን አቶ አበረ የሞቱበትን ትክክለኛ ምክንያት ማወቅ አለማቻሉን ምንጮች አመልክተዋል።

ይሁንና፣ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በኮሚሽነር አበረ አዳሙ ህልፈት የተሰማውን ሐዘን በመግለፅ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ “የቀድሞው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ባጋጠማቸው ድንገተኛ ህመም በህክምና ሲረዱ ቢቆይም ሊሻላቸው ባለመቻሉ ሚያዚያ 26/2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል” ሲል አስታውቋል።

በተያያዘ፣ አቶ አበረ አዳሙ በድንገተኛ ህመም ህይወታቸው ማለፉን የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሐኪም ተናግረዋል

“አቶ አበረ አዳሙ ሕይወታቸው ያለፈው በህክምና ላይ እያሉ ነበር” ያሉት ሐኪሙ፣ ከድንገተኛ ሕመሙም ሆነ ከክስተቱ ጋር የተያያዙ ተግባራትን እያከናወኑ በመሆኑ ለጊዜው ዝርዝር መረጃ ለመስጠት አለመፈጋቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር መሰረት ደባልቄ በበኩላቸው “ኮሚሽነር አበረ ዛሬ ጠዋት ልቤን አመመኝ ብለው ወደ ሆስፒታል ሄደው በህክምና ላይ እንዳሉ ህይወታቸው አልፏል” በማለት የኮሚሽነር አበረ አዳሙ አስክሬን ለተጨማሪ ምርመራ ወደ አዲስ አበባ መላኩን አስታውቀዋል።

LEAVE A REPLY