“የቀድሞውን የባህር ኃይል ዝና መልሰን እንገነባለን” ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ደብረዘይት በሚገኘው የመከላከያ ኢንጂነሪነግ ኮሌጅ ግቢ ዛሬ በተከናወነው መርሃ ግብር፣ የፈረሰውን የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል መልሶ የመገንባት ስራ መጀመሩ ይፋ ተደረገ።
የባህር ሀይሉ አዲስ አርማ፣ የደንብ ልብስ እና ቢልቦርድ ምርቃት እንዲሁም ባህር ሀይሉ ለሚያስገነባው መሰረታዊ የባህረኞች ስልጠና ማዕከል የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ ስርዓት ተከናውኗል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላ፣ የባህር ሀይል አዛዥ ሬድ አድሚራል ክንዱ ገዙ፣ የሰራዊቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ የውጭ አገራት አታሼዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተከናወነው በዚሁ ፕሮግራም፣ የተመረቀው አዲሱ የባህር ኃይል ዓርማ፤ ቀይ፣ ነጭና ቢጫ ቀለማትን መያዙና ቀዩ መስዋዕትነትንና ዝግጁነትን፣ ነጩ ሰላምን፣ እውቀትን፣ ላብና የመለያ ክብርን እንዲሁም ቢጫው ለሀገርና ለህዝቦች መጪው ጊዜ የብሩህ ተስፋ ዘመን መሆኑን የሚያመላክት መሆኑ ተመልክቷል።
በአርማው ላይ የባህር ኃይል ዓለምአቀፍ ምልክት የሆነው መልህቅ እና በቀላሉ የማይበገር የባህር ኃይል በተሰማራበት ቀጠና ላይ የሚሰጠውን ግዳጅ በብቃትና በጥንካሬ እንደሚወጣ የሚያሳየው የወይራ ዘለላም የተቀመጠበት ሲሆን፣ በአርማው ላይ ያለው ሰማያዊ መደብ ባህር ኃይሉ ተልዕኮውን የሚወጣው በባህርና በውቅያኖስ ላይ መሆኑን ሲያሳይ ሰንደቅ አላማው ደግሞ ለሀገርና ለሰንደቅ አላማ ዘብ መቆምን እንደሚያሳይና አርማው በጠቅላይ መምሪያው፣ በመርከቦችና በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይ ጥቅም ላይ እንደሚውልም ተገልጿል።
ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ባስተላለፋት መልእክት “ኢትዮጵያ ጠንካራና ስመጥር የሆነ ባህር ሀይል የነበራት ቢሆንም አሳፋሪ በሆነ መልኩ እንዲፈርስ ተደርጓል። ከሁለት ዓመት ወዲህ የለውጡ መንግሥት በሰጠው ትኩረትና በመከላከያ ድጋፍ የባህር ሀይሉ በመሰረታዊ ደረጃ ሊመሰረት ችሏል። በቀጣይም በተጠናከረ ስራና እገዛ ኢትዮጵያ ወደቀድሞው የባህር ሀይል ስምና ዝናዋ ትመለሳለች” ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በማያያዝም “ኢትዮጵያ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን። እነዚህ ጠላቶች አገሪቷን በማዳከም ከችግር እንዳትወጣ፣ ታላቅነቷን አስጠብቃ እንዳትሄድ እየሰሩ ነው” ያሉት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ “ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው የተነሱባት አገር ናት፤ ይህ ሁሉ ትንኮሳ፣ ማናቆርና ህብረተሰቡን እርስ በእርሱ ማባላት ኢትዮጵያን ለማዳከም ነው። ሲሉ ተደምጠዋል።
ፍላጎታቸው ሀገሪቷ ስትዳከም ባላት ሃብት እንዳትጠቀም ማድረግ ነው። ከ100 ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰሩ ኃይሎች ዛሬ ተጠናክረው አገራችን ላይ ዘምተዋል። ባንዳዎችን ይዘው አገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ያሉትን እነዚህን ኃይሎች በውጭ ወራሪ እንደማንቻል ስለሚያውቁ ከውስጣችን ሊያፈራርሱን ያስባሉ። ህዝቡ ከሰራዊቱ ጎን በመቆም የተደገሰውን ለማክሸፍ መታገል ይኖርበታል” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።