ኢትዮጵያ ነገ ዜና:- በአሶሳ ከተማ በሚገኘው መንበረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ግቢ ውስጥ፣ ከ35 ዓመታት በላይ ተቀብሮ የኖረ ከ624 በላይ ተተኳሽ ጥይት፣ ቦታው ለልማት ስራ ሲቆፈር ከትናንት በስቲያ መገኘቱን የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት አስታውቋል።
የአሶሳ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መልዓከ ጸሀይ ቆሞስ አባ ዘካርያስ ጸጋው “አካባቢው ከዘመነ ደርግ በፊትም ሆነ በኋላ የጦር ሰፈር ነበር። የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ማከማቻ ቦታም ነበር። ከሚመለከተው የመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር ቦታው ለቤተ-ክርስቲያን አምልኮት ተሰጥቷል ብለዋል።
ቤተክርስቲያኗ ቦታውን አስከብራ በመቆየቷ ከ35 አመት በላይ ተቀብሮ የቆየ ጥይት በዚህ መንገድ የተገኘ መሆኑንም ህብረተሰቡ ሊያውቅ ይገባል” ማለታቸውንም ጽ/ቤቱ ገልጿል።
የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮ/ር ቡሽራ አልቀሪብ በበኩላቸው “ቦታው ለቤተክርስቲያን ልማት ከመዋሉ በፊት የደርግ 47ኛ ክፍለ ጦር የነበረበት ቦታ ነው፤ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ማከማቻ ሰፈር ነበር። አሁን የተገኘው ተተኳሽ ጥይት በቁጥር 624 በላይ የሚሆንና ከ35 ዓመት በላይ በመሬት ዉስጥ ተቀብሮ የተገኘ የበሰበሰ እና አገልግሎትም የማይሰጥ ነው። አካባቢው የቀድሞ ጦር ሰፈር መሆኑን በመረዳት ህብረተሰቡ እውነቱን ሊረዳ ይገባል፤ ሁኔታውንም በሌላ መንገድ ሊወስደው አይገባም” ሲሉ ስለጉዳዩ መግለጫ መስጠታቸውንም የአሶሳ ከተማ አስተዳድር ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት አስታውቋል።