ፓርላማው “የህወሓት እና ሸኔን አሸባሪነት” በአብላጫ ድምጽ አፀደቀ!

ፓርላማው “የህወሓት እና ሸኔን አሸባሪነት” በአብላጫ ድምጽ አፀደቀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና:- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከቀናት በፊት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ሁለቱ ቡድኖች በአገር እና በህዝብ ላይ የሽብር ተግባራትን በመፈፀም ላይ በመሆናቸው በሽብርተኝነት መፈረጃቸው አግባብ መሆኑን ጠቅሶ “ሕወሐትና ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።

ጉዳዩን ለማየት የተሰየመው ፓርላማ በዛሬ ውሎው “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ በቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተወያይቶ በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁ ታውቋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዚያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው “የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 18 እና 19 መሠረት “ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” የሽብር ወንጀልን ዓላማቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ በመሆኑና የድርጅቶቹ የሥራ አመራር ወይም ውሳኔ ሰጭ አካላት ወንጀሉን አምነው የተቀበሉት ወይም አፈጻጸሙን እየመሩት በመሆኑ፤ የሽብር ተግባር መፈጸምም የድርጅቶቹ ጠቅላላ መገለጫ በመሆኑ፤ ድርጅቶቹ በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲሰየሙ ሲል” የውሳኔ ሐሳቡን ለፓርላማ ልኳል።

የውሳኔ ሃሳቡ የቀረበለት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤትም ድርጅቶቹ “ሽብርተኛ” መባላቸውን ለመቃወም የሚያስችል ማስረጃ ካላቸው ለምክር ቤቱ እንዲያቀርቡ የጥሪ ማስታወቂያ ስለማውጣቱ በተከታታይ መዘገባችን ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዛሬ በሽብርተኝነት የተፈረጀውና መንግስት “ሸኔ” በሚለው ነጠላ ስም ብቻ የሚጠራው ቡድን ማንነት በርካቶችን ግራ ሲያጋባ የቆየና ብዙዎችም “ሸኔ እያለ እራሱን የሚጠራ ድርጅት በሌለበት እንዴት አሸባሪ ተብሎ ይሰየማል?” የሚል ጥያቄ ሲያሰሙ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የተጠየቁት የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዮስ ዛሬ ምላሽ ሰጥተውበታል።

“በተለምዶ ሸኔ የሚባለው እራሱን ደግሞ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን ነው። በምዕራብ ኦሮሚያና በሌሎችም ክልሎች እየተንቀሳቀሰ ጥቃት የሚያደርስ ድርጅት ነው። እራሱ ለእራሱ የሰጠውን ስያሜ ግን እኛ የምናፀድቅበት ምክንያት የለንም፤ ተገቢም አይሆንም ብለን እናምናለን ሲሉ አብራርተዋል።

ይህ ቡድን ከዚህ በፊት እንደ ‘ህወሓት’ ተመዝግቦ ፣ ህጋዊ እውቅና ፣ ህጋዊ ሰውነት እና ሰርተፊኬት ኖሮት የሚያውቅ አይደለም፤ ስለዚህ ስያሜው እሱ እራሱን በአንድ ስያሜ ይሰይማል፤ አንዳንዶች በሌላ ስም ይጠሩታል። በተለምዶ ‘ኦነግ ሸኔ’ ይባል ነበር ስለዚህ በተለምዶ ከሚጠራበት ‘ኦነግ ሸኔ’፣ ‘ሸኔ’ የሚለውን መርጠናል” ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶ/ር ጌድዮን
“እዚህ ጋር ግልፅ መሆን ያለበት በአዋጁ አንቀፅ 23 መሰረት ስያሜውን ብትለዋውጥ ያው ቡድን ያው ስብስብ እስከሆነ ድረስ፤ በውሳኔ ሀሳቡ የተገለፀው ስብስብ እስከሆነ ድረስ ስያሜ መለዋወጥ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ውሳኔ ሀሳቡ ተፈፃሚ ይሆንበታል” በማለት ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

LEAVE A REPLY