ኢትዮጵያ ነገ ዜና:- የዘንድሮውን የፊቼ ጫምባላላ በዓል የኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋትን ለመከላከል ሲባል በአደባባይ እንደማይከበር ያስታወቁት የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የዘንድሮው የሲዳማ ህዝብ ዘመን መለወጫ “ፊቼ ጫምባላላ” በዓል፣ ከንክኪ በራቀ መልክ ዛሬ ሚያዝያ 29 መከበር መጀመሩንና ነገ ሚያዝያ 30ም እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመርዳትና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ሊሆን እንደሚገባውም ርዕሰ መስተዳደሩ ዛሬ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ገልጸዋል።
የሲዳማ ህዝብ ዘመን መለወጫ የሆነው ፊቼ ጫምባላላ፣ ከጥንት ጀምሮ ሲከበር የቆየ መሆኑን አስታውሰው “በዓሉ የተጣሉትን በማስታረቅ ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና ለሰው ልጆችና እንስሳት ክብር በመስጠት የሚከበር ታላቅ በዓል ነው” ብለዋል።
“ለበዓሉ ሲባል እንስሳት የማይታረዱበትና በቀያቸው በእንክብካቤ የሚያሳልፉበት እንዲሁም ዛፍ የማይቆረጥበት በመሆኑም እለቱን ልዩ ያደርገዋል” ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ በአሁን ወቅት በፍጥነት እየተዛመተና በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያሰከተለ ባለው የኮሮና ወረርሽኝ ተዕዕኖ ምክንያት በዓሉ እንደወትሮው በአደባባይ በመሰባሰብ እንደማይከበር ገልፀው፣ ሆኖም በዓሉ ባህላዊ ትውፊቱን ሳይለቅ ዘንድሮ ሁሉም የብሄሩ ተወላጅ በየቤቱ ሆኖ የሚያከብረው መሆኑን አመላክተዋል።
ህብረተሰቡ የዘንድሮውን ፊቼ ጫምባላላ በአልን ሲያከብር እራሱን ከኮሮና ወረርሽኝ በመከላከል ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተለይ ከተጣላው ጋር ይቅር በመባባልና ከመዋደድ ባሻገር እርስ በእርስ በመደጋገፍ እንዲሆንም አቶ ደስታ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።