ኢትዮጵያ ነገ ዜና:- “Long March 5B” የተሰኘው የቻይና ሮኬት ግዙፍ አካል ከህዋ ወደ መሬት በፍጥነት እየተምዘገዘገ መሆኑ ተነግሯል።
“መሬት ላይ ሲወድቅ የት አካባቢ ሊያርፍ ይችላል?” የሚለው ጉዳይ ብዙዎችን እያሳሰበ የሚገኝ ሲሆን፣ በተያዘው ሳምንት ምድር ላይ ያርፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ እየተነገረ ይገኛል።
ከቻይናው ሮኬት የተገነጠለ ነው የተባለው ይህ ግዙፍ አካል ወደ ታችኛው የአየር ንፍቀ ክበብ ለመግባት በመሬት ዙሪያ እየተሽከረከረ እንደሚገኝ የተነገረ ሲሆን፣ አሜሪካ የዚህን ግዙፍ የሮኬት አካል ጉዞ እየተመለከተች መሆኑን ብትገልፅም መትታ የመጣል እቅድ እንደሌላት አስታውቃለች።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስተን ማንንም የማይጎዳበት ስፍራ ያርፋል ብለን ተስፋ እናደርጋልን፤ ይህም ውቅያኖስ ወይም ሌላ ስፍራ ሊሆን ይችላል ሲሉ ነው የገለፁት።
የቻይና መገናኛ ብዙሃን ባለፉት ቀናት “የሮኬቱ ግዙፍ አካል ሰዎች በማይኖርበት አካባቢ ይወድቃል” የሚለውን ሃሳብ ውድቅ ሲያደርጉ እንደነበረ ሲሆን፣ ብዙዎች የሮኬቱ አካል ወደ ዓለም አቀፍ የውሃ አካል እንደሚወድቅ ነው ግምታቸውን አስቀምጠዋል።