የቅዱስነታቸውን መግለጫ በተመለከተ || ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ

የቅዱስነታቸውን መግለጫ በተመለከተ || ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ

* የቅዱስነታቸውና የብፁዓን አባቶች ደኅንነት ያሳስበኛል፣
* መንግሥት ጥበቃ ያድርግላቸው፣
* ምእመናን እንረጋጋ!!
++++
ቅዱስ አባታችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በስልክ የተቀረጸ የቪዲዮ መልእክታቸው በTMH፣ የጽሑፍ ዘገባቸው ደግሞ በAP ተለቅቆ ተመለከትነው። ሁለቱም እኩል የተለቀቀው maximum effect እንዲኖረው ተደርጎ ነው። የታሰበውን ግብ የመታ ይመስላል።

ቅዱስነታቸው በተለይም በትግራይ ጉዳይ በሰጡት አስተያየት የትግራይ ሕዝብ ላይ እልቂትና ብዙ ወንጀል እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል። ይህንን ሐሳባቸውን ለማካፈል ብዙ ጊዜ ሞክረው እንደተከለከሉም አብራርተዋል። (በዚሁ ሰበብ አንዳንድ ባለጌዎች የጭቃ ጅራፋቸውን በቅዱስ አባታችን ላይ ማላቀቅ ሲጀምሩ ሌሎቹ ደግሞ “ንግዳችን ደራ”ብለው እልል በቅምጤ ይዘዋል። እግዚአብሔር ይመልከተው።) እኔ ግን ብዙ ሥጋት፣ እና ብዙ ጥያቄዎች አሉኝ።

መግለጫው ዛሬ፣ ከAP ጋራ በተናበበ ሁኔታ መለቀቁ፣ የመስቀል አደባባዩ ጉዳይ (በሙስሊሞችና በክርስቲያኖች መካከል?) መቀስቀሱ፣ ከዚህ ቀደም ብሎ ብዙ የሕወሓት ሰዎች “አዲስ አበባ ላይ ችግር እንፈጥራለን” ማለታቸው፣ አባ ሰረቀ የተባሉ የአውስትራሊያ መነኩሴ “አዲስ አበባ እንደ ባቢሎን ትፈርሳለች” ማለታቸው ወዘተ የአጋጣሚ ብቻ አልመሰለኝም። ምንድነው የታቀደልን? ምንስ ማድረግ አለብን?

ለጊዜው በአፋጣኝ መደረግ ያለበት ነገር ቢኖር የቅዱስነታቸው ደኅንነት እና ጥበቃ መጠናከር ነው። እግዚአብሔር ያርቀው፣ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱ ሰዎች በአባቶቻችን ላይ አደጋ አይጥሉም ብዬ አላስብም። በዚህ ሳምንት ሰኞ በአደባባይ ሚዲያ በቀረብኹበት ሰዓት እንዳልኩት “ልክ ኮሚሽነር አበረ እንደሞቱት፣ ሐጫሉ ሁንዴሳ እንደተገደለው” ያለ ታዋቂ ሰዎች ላይ ሊፈጸም የሚችል ጥቃት ያሰጋኛል። (በውጪ ሀገር ሰላዮች፣ በእኛው ባንዳዎች ሊፈጸም ይችላል። ሕዝቡ መንግሥት ላይ እንዲነሣ። ሀገራችን ወደለየለት ቀውስ እንድትገባ።)

ቅዱስነታቸውን በተመለከተ የቤተ ክህነቱ ጥበቃ ከመንግሥት ጋራ ሆኖ ጉዳዩን በጥብቅ መያዝ አለበት። መንግሥትም ትክክለኛ security detail ማዘጋጀት አለበት። የታሰበልን ከባድ ይመስላል። እግዚአብሔር ይሰውረን።

እስከዛው ግን፣ በቅዱስ አባታችን ላይ የማይገባ ንግግር የሚናገሩ ባለጌዎችን አፋቸውን እንዲሰበስቡ ማድረግ ይገባል። እናንት ባለጌዎችና የሞት ነጋዴዎች፣ የምታተርፉት እርግማን ብቻ ነው። ያውም ለልጅ ልጆቻችሁ የሚደርስ እርግማን።

ማጠቃለያ:-

1. ሕዝበ ክርስቲያኑ በተረጋጋ መንፈስ ነገሮችን በሰከነ መንገድ ቢመለከት፣
2. ቋሚ ሲኖዶሱ አስቸኳይ መግለጫ ቢሰጥ፣
3. የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ከቋሚ ሲኖዶሱና ከቅዱስነታቸው ጋራ በአስቸኳይ ውይይት ማድረግ ቢችሉ፣
4. የቅዱስ ፓትርያርኩ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ብፁዓን አባቶችም ደኅንነት እንዲጠበቅ ቢደረግ፣
5. ቅዱስ ፓትርያርኩን የሚያስጨንቃቸው እና የሚያፍናቸው አካል ካለ በአስቸኳይ እንዲቆምና ልኩን እንዲያውቅ ቢደረግ፣
6. በሚዲያዎች የሰጧቸውና ታፈኑ የተባሉት መግለጫዎች ይለቀቁና ሕዝብ ይያቸው። ፍርድ የተመልካች ነው። ታፍነው የቀሩ አሉ መባሉ የሚያመጣው ጣጣ ብዙ ነው። ደግሞስ የፓትርያርክን ሐሳብ “ለማፈን” የሚችል ማን ይኖራል?
7. ከዚህ በፊት በአደባባይ ሚዲያ ደጋግመን እንደተናገርነው ቤተ ክህነቱ (ከሎሎች ቤተንእምነቶችም ጋራ ሆኖ፣ ከተቻለ) fact finidinf mission/ አጣሪ ልዑክ የማይልከው ለምንድር ነው? አደጋውን በስማ በለውና ከፈረንጅ አፍ ሳይሆን ለምን ራሳቸው አያጣሩም ሔደው?
8. ለማንኛውም ይህንን የቤተ ክህነት ምስቅልቅል ቶሎ መፍታት ካልተቻለ ቤተ ክርስቲያናችንን ለመበጥበጥ ብዙ ሲሞክሩ ለነበሩት የሕወሓት ጋሻ ጃግሬዎች ትልቅ በር ይከፈትላቸዋል የሚል ሐሳብ አለኝ።

ኢታርእየነ ሙስናሃ ለኢትዮጵያ!!!!

LEAVE A REPLY