ፌደራል ፖሊስ “የሸኔን እንቅስቃሴ የማምከን ዘመቻ” መጀመሩን አስታወቀ!

ፌደራል ፖሊስ “የሸኔን እንቅስቃሴ የማምከን ዘመቻ” መጀመሩን አስታወቀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና:- የአሸባሪው ሸኔን እንቅስቃሴ ለማምከን የፌደራል ፖሊስ አባላት በወለጋ ሆሮ ጉድሩ ዞን ተሰማርተው፣ ከአካባቢው ሚሊሻና ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት እየሰሩ መሆኑ ተገለፀ፡፡

በዞኑ የሚንቀሳቀሰውን የሸኔ ቡድን በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችን በመግደል፣ በማፈናቀል፣ ንብረት በማውደምና በመዝረፍ አካባቢውን የሽብር ቀጠና ለማድረግ የሚሰራውን ስራ ለመግታትና ለማስቆም፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ስምሪት በመስጠት የፖሊስ አባላቱ ወደ ወለጋ ሆሮ ገድሩ ዞን ገብተው የአሸባሪውን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ለማስቆም የላቀ ሚና እየተወጡ እንደሚገኙም ፖሊስ አስታውቋል።

በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራ ልዑክ፣ ወደ አካባቢው በመሄድ በቦታው በግዳጅ ላይ ካሉ አባላት እንዲሁም ከአካባቢው አስተዳደር ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸው አያይዞ የገለፀው ፖሊስ፣ በውይይቱም በዞኑ ሰላም ለማስፈንና የሸኔን ህግ ወጥ እንቅስቃሴ ለማስቆም በአካባቢው አስተዳደር ውስጥ ያሉ ችግሮችን በአግባቡ መፈተሽና መለየት እንደሚገባ መነሳቱን አመልክቷል፡፡

በወለጋ ሆሮ ጉድሩ ዞን ግዳጅ ላይ የተሰማሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ ከአካባቢው አስተዳደርና የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩ ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለፃቸውንም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

LEAVE A REPLY