ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5፣ በአንድ ግለሠብ መኖሪያ ቤት ውስጥ የተደበቁ ከ4 ሺህ በላይ የተለያዩ ጥይቶች እና አንድ ሽጉጥ በፖሊስ እና በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ቅንጅት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የከተማዋን ብሎም የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ እኩይ አላማ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች የጦር መሳሪያዎችን በህገ ወጥ መንገድ ከቦታ ቦታ ሲያዘዋውሩ በህዝብ ጥቆማ እና በፀጥታ አካላት ክትትል በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሚገኙ ተገለጿል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለዚሁ ሀገርን የማፍረስ አላማ ሲንቀሳቀስ የነበረ አንድ ተጠርጣሪ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ጎፋ ኢንዱስትሪ መንደር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመኖሪያ ቤት ደብቆ ያስቀመጣቸው 3007 የማካሮቭ ሽጉጥ፣1320 የብሬን እና 05 የክላሽንኮቭ በአጠቃላይ 3ሺ 332 ጥይቶችን እንዲሁም አንድ ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ በተጨማሪም ባዶ የጥይት ማሸጊያ ሳጥኖች ተገኝተዋል።
ሁሉም ከህዝብ በተገኘ ጥቆማ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በቅንጅት ባደረጉት ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
በተጠርጣሪው ላይ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥም በመረጃ ስልክ ቁጥሮች 0111110111 ወይም በ991 ነፃ የስልክ መስመር ደውሎ ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል።