ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ የስዊዝ ቦይ አካል የሆኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ባስመረቁበት በዛሬው ዕለት “በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ግብጻውያን ሊታገሱ ይገባል” በማለት ተናግረዋል።
ለህዝባቸው ባደረጉት በዚሁ የአደባባይ ንግግራቸው “በግድቡ ጉዳይ መስጋታችሁ ተገቢ ነው። ነገር ግን ልትታገሱ ይገባል፤ ድርድር ጊዜ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ የግድቡ ድርድር ጉዳይ ጊዜ፣ ትዕግስት እና ጥንቃቄን የሚፈልግ እንደሆነ አመልክተዋል። ከግድቡ ጋር በተያያዘ የተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በማስታወስም እልባት ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት አል ሲሲ፣ ከወር በፊት የስዊዝ ቦይ መተላለፊያ “ኤቨር ጊቭን” ከተሰኘች እቃ ጫኝ መርከብ ጋር በተያያዘ እንዲዘጋ በተደረገበት ጊዜ በአካባቢው ተገኝተው ባደረጉት ንግግር “ከግብጽ የውሃ ድርሻ ላይ ማንም አንዲትንም ጠብታ ሊነካ አይችልም” የሚል ጠንካራ መልዕክት ያለው ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡