ኢትዮጵያ “በጎዳና ላይ ኢፍጣር” ሪከርድ ሰበረች!

ኢትዮጵያ “በጎዳና ላይ ኢፍጣር” ሪከርድ ሰበረች!

1442ኛው ዒድ አል ፈጥር በዓል ነገ ይከበራል!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– 1ሺህ 442ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል ነገ ሐሙስ እንደሚከበር የገለፁት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ሃላፊ ሀጅ ኡስማን አደም “የሸዋል ወር ጨረቃ ትናንት ባለመታየቷ 1 ሺህ 442ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል ነገ ሐሙስ ይከበራል” በማለት ለህዝበ ሙስሊሙ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።  የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ኡመር ኢድሪስ በበኩላቸው “ምዕመናን በዓሉን ሲያከብሩ የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

በተያያዘ፣ “ዒድ አል ፈጥር’ በቅዱሱ ረመዳን ወር መጨረሻ እና በሻወል ወር የመጀመሪያ ቀን ላይ የሚውል የጾም ወር ማጠናቀቂያ ታላቅ በዓል ነው። ሕዝበ ሙስሊሙ ወሩን ሙሉ በጾምና በስግደት፣ እንዲሁም በመልካም ተግባራት አሳልፎ ከፈጣሪ የመጨረሻውን ምንዳዕ የሚቀበልበት ልዩ ቀን ነው።

በዒድ ዕለት ሕዝበ ሙስሊሙ ሰብሰብ ብሎ የዒድ ሶላት ይሰግዳል። ይሄም የመሆኑ ምክንያት በመሰባሰብ ውስጥ አንድነት፣ በመሰባሰብ ውስጥ ኅብረት፣ በመሰባሰብ ውስጥ ጥንካሬ መኖሩን ለማመልከት ነው። ለብቻ ከሚሰገደው በላይ በጀምአ መስገድ ከአላህ ብዙ እጥፍ ምንዳዕ እንደሚያስገኝ በእስልምና ይታመናል። “የአላህ እጅ ሰብሰብ ባሉ ሰዎች መሐል ይገኛል” ሲል የእምነቱ አስተምህሮም ያስረዳል” በማለት ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ በአሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ገልፀዋል።

“የዘንድሮውን ዒድ አል ፈጥር የምናከብረው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በርካታ ፈተናዎች እንደተደቀኑባት እያስታወስን ነው። መዋኛችን ድፍርስ፣ መንገዳችን እሾህ የበዛበት መሆኑን እናውቃለን። በመንገዳችን ላይ እንቅፋቶችን የሚያኖሩ፣ ወደኋላ የሚጎትቱ፣ ተስፋችንን ሳናይ በፊት ተሰብረን እንድንወድቅ መሠረታችንን የሚገዘግዙ ኃይሎች፣ ከውጭም ከሀገር ውስጥም በርትተው የመጡበት ፈታኝ ጊዜ ነው” ያሉት ጠ/ሚ/ሩ “ተገዳዳሪዎቻችን ምንም ያህል ቢለፉ ጸንተን ለመቆም መወሰን አለብን። ክፉውን ጊዜ እንደ ዒድ ሶላት ሰብሰብ ብለን ልንጋፈጠው፣ የአንድነታችንን ልክ አሳይተን ልናልፍ ይገባል። በኅብረታችን የሚገጥሙንን ፈተናዎች እንደ ምንሻገራቸው ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያን እድል በእኛው እንጂ በሌላ በማንም እጅ እንዳልሆነ ለዓለም ማሳየት ይኖርብናል” ብለዋል።

በመልዕክታቸው ማጠቃለያም “ጠብን ለሚዘሩ፣ ከሌሎች ወንድም እኅቶቻችን ጋር ግጭት ለሚጠነስሱ፣ ቁስላችንን በማከክ ለሚያደሙ ዕድል አንስጣቸው። እኛ ከፍቅር እነርሱ ከጠብ፣ እኛ ከአንድነት እነርሱ ግን ከመለያየት፣ እኛ ከድልድይ እነርሱ ግን ከአጥር፣ እኛ ከሀገር እነርሱ ግን ከመንደር እንደምናተርፍ አንርሳ። ለዛሬ ብለን ነገን ከምናበላሽ፣ ለነገ ስንል ዛሬን እንሠዋ። የሰላም፣ የደስታ፣ የተስፋና የበረከት ዒድ እንዲሆን ተመኘሁ” ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአዲስ አበባ ከሜክሲኮ አደባባይ እስከ ባምቢስ በተዘረጋው ረጅም መንገድ “ታላቅ የጎዳና ላይ ኢፍጣር በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ትናንት የተከናወነው ስነ ስርዓት፣ የአለምን ክብረወሰን መስበሩ እየተነገረ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤም “የኢፍጣር ክብረወሰን የኢትዮጵያ ነው!! እንኳን ደስ አለን!” ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ይህንኑ አረጋግጠዋል።

“ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር በኢትዮጵያ” በሚል ትናንት በተከናወነውና 5 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ በሸፈነው የጎዳና ላይ ኢፍጣር ስነስርዓት፣ ከአዲስ አበባ ከተማና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ 1 ሚሊዮን ዜጎች እንደተሳተፉ የተገመተ ሲሆን፣ በዚህም ከዚህ ቀደም (በ2011) በግብፅ ተይዞ የነበረው የኢፍጣር ሪከርድ መሰበሩ ተመልክቷል።

በ2011 (እአአ) በግብጽ በተከናወነውና 3.1 ኪሎ ሜትር ርዝመት በነበረው የጎዳና ላይ ኢፍጣር ስነ ስርዓት 7 ሺህ ሰዎች መሳተፋቸውና ይህም የአለም ሪከርድ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ነገ ዝግጅት ክፍልም ለመላው ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን “እንኳን ለ1442ኛው ዒድ አል ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!” በማለት መልካም ምኞቱን ይገልፃል።

LEAVE A REPLY